የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ፈቲህያ አደን ፣ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና የምክር ቤቱ ጸሀፊ የተከበሩ አቶ ስንታየሁ ማሞ ለምክር ቤቱ ተጠሪ ከሆኑት ተቋማት መሀል በሆነው በድሬዳዋ ብዙሀን መገናኛ ድርጅት ጉብኝት አድርገዋል፡፡ የተከበሩ የምክር ቤቱ አመራሮች የተቋሙን የተለያዩ የስራ ክፍሎች በብዙሀን መገናኛ ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱሰላም መይደኔ አስጎብኚነት ተዟዙረው የጎበኙ ሲሆን በመጨረሻም ለተቋሙ የማኔጅመንት አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱም በድርጅቱ የማኔጅመንት አባላት ተቋሙ ስለሚገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በተለይም ተቋሙን በሙሉ አቅሙ ስራዎችን መስራት እንዳይችል ተግዳሮት የሆኑበት የፋናንስ ችግር፣ የስራ ቦታ ምቹ ያለመሆን፣ የግብአት አለመሟላት፣ የተሸከርካሪ እጥረትና የትኩረት አለማግኘት ጉዳዮች የተጠቀሱ ሲሆን በምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ በተሰጠው ምላሽም ተቋሙ የድሬዳዋን ገጽታ ለመገንባት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው በምክር ቤቱ በኩል ተቋሙ የሚገኙበትን ችግሮች በሂደት ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ እና ምክር ቤቱ ተቋሙን መደገፍ ባለበት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡


