አሜሪካ እና ኢራን ሆርሙዝን ለመክፈት መስማማታቸውን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።
አሜሪካ እና ኢራን ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የኢራን መንግሥት ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ “ሁለትዮሽ የተኩስ አቁም” ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል።
በስምምነቱ መሰረትም ኢራን ለዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦች ዝግ አድርጋው የነበረውን የሆርሙዝ ወሽመጥ ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ክፍት ታደርጋለች።
ይህ ድንገተኛ ዲፕሎማሲያዊ ለውጥ የመጣው በፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሸሪፍ አደራዳሪነት ሲኾን ሁለቱ ወገኖች በመጭው አርብ በኢስላማባድ በሚጀመረው ውይይት ላይ ይሳተፋሉ።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና ድልድዮች ላይ ሊሰነዝሩት የነበረውን ከፍተኛ የአየር ጥቃት ለጊዜው አግደዋል።
እስራኤልም በዚህ የተኩስ አቁም ስምምነት መካተቷን ከዋይት ሃውስ የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ በሰጡት መግለጫ፣ በኢራን ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች እስከቆሙ ድረስ የኢራን ጦር ኀይልም የመከላከል እርምጃውን እንደሚያቆም ገልጸዋል። ይሁን እንጂ በወሽመጡ የሚያልፉ መርከቦች በኢራን ወታደራዊ ቁጥጥር ስር ኾነው የደኅንነት ቅንጅት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
ይህ ስምምነት ላለፉት አምስት ሳምንታት ቀጥሎ የነበረውን ጦርነት ለማርገብ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እንደ መልካም አጋጣሚ ተወስዷል። በዜናው ሳቢያም የዓለም የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ ተዘግቧል።
ምንጭ:- የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ፣ አዲስ ሚዲያ ኔቶርክ እንዲሁም ከሌሎች ዓለም አቀፍ የመረጃ ምንጮች


