በስፍራው እየተገነባ የሚገኘው የዳንወዳግ የገበያ ማዕከል አክሲዮን ማህበር ሊቀመንበር ሀጂ መሀመድ አረጋ እንደገለጹት፤ የእሳት ቃጠሎ አደጋው ከደረሰበት ማግስት አንስቶ ከተጎጂዎችና ከመንግስት አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ በማዋቀር በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በተለይም ነጋዴዎችንም ሆነ አካባቢውን መልሶ የማልማትና የግንባታ ሂደት ግልፅነት፣ ኃላፊነትና መናበብ በተሞላበት መልኩ እንዲመራ መደረጉን አስረድተዋል።
በሀገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ ወገኖች የተገኘውን የገንዘብ ድጋፍ በተመለከተም፣ የተቋቋሙት ኮሚቴዎችና ተጎጂዎቹ በጋራ በተስማሙበት መንገድ፣ አቅም በፈቀደ መልኩ እንዲከፋፈል መደረጉን ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል።
አሁን ላይ ከአንዳንድ ወገኖች እየተናፈሱ ያሉ የተሳሳቱ መረጃዎች እውነትነት የሌላቸውና አፍራሽ ከመሆናቸው ባለፈ፣ ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት እየጣሩ ያሉ አካላትን የማይያበረታቱ መሆኑን ሀጂ መሀመድ አብራርተዋል።
የዳንወዳግ የገበያ ማዕከል የቦርድ አባል የሆኑት ሀጂ ሁሴን ከድር በበኩላቸው፥ “የተቃጠለው ንብረታችን እንጂ አካውንታችን (መስራት የምንችልበት አቅማችን) አልተቃጠለም” በማለት ተስፋ ሰጪ መልዕክት አስተላልፈዋል። በአሁኑ ወቅት አካባቢውን በአዲስና ዘመናዊ መልኩ የመገንባት ስራው ተፋጥኖ 25 በመቶ አፈፃፀም ላይ መድረሱንም ይፋ አድርገዋል።
የቦርዱ አባሉ አክለውም፥ አስተዳደሩ የግንባታ ቦታውን በነፃ በማመቻቸትና በማንኛውም ሁኔታ ከጎናቸው በመሆን ላደረገውና እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በድሬዳዋ አስተዳደር የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሲኒየር ኤክስፐርት አቶ ሸምሸዲን መሀመድ እንደገለጹት፤ አደጋውን ለመቋቋም ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰብ አንዱ ነው።
ቃል የተገቡና ገቢ ያልተደረጉትን ሳይጨምር፣ እስካሁን (እስከ 2018 ዓ.ም) 37 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር መሰብሰብ ተችሏል።
በየዘርፉ በተቋቋሙ ኮሚቴዎችና ከተጎጂዎች ጋር በተደረሰ ስምምነት መሰረት፥ ለ447 ግለሰቦች ከደረሰባቸው ውድመት የ13 በመቶ ድርሻ እኩል ድጋፉ እንዲከፋፈል ተደርጓል።


