ከድሬዳዋ አስተዳደር እና ከድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የተሰጠ መግለጫ.

    ትላንት ማታ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንፁሃን ዜጎች ላይ በደረሰው እጅግ አሰቃቂ የወገን ህይወት መጥፋት የድሬዳዋ አስተዳደር፣ የድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት እና ነዋሪዎች እጅጉን አዝነናል፤ በሰላማዊና ንፁሃን ዜጎች ላይ በደረሰው አረመኔያዊና ዘግናኝ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ልባችንም ክፉኛ ተሰብሯል፡፡
    እኛ ኢትዮጵያዊያኖች ጠላት ያልደፈረን፤ ሰብዓዊ ክብራችንን ያላሳጣን ህዝቦች ሆነን ሳለ በየጊዜው በአካባቢና በማንነት ላይ ያተኮረ እጅግ ዘግናኝና አሰቃቂ የጥፋት ድርጊቶች ግን ኢትዮጵያዊ ክብራችንን የማይመጥንና የሰውነት ባህሪ የጎደለው ክፉ አድራጎት ነው፡፡
    ይህ በሰላማዊና ንፁሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰው ጥፋትና እልቂት እንዳይደገም ብሎም በዚህ አረመኔያዊ ጥፋት ላይ የተሳተፉ አካላትን መንግስት በአስቸኳይ ህግ ፊት በማቅረብ ፍትህ እንዲሰፍን የድሬዳዋ አስተዳደር ጥሪ እያቀረበ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ አስተዳደሩ የሚጠበቅበትን ሚና ከመወጣትም ባሻገር የፌደራል መንግስትና የክልሉ መንግስት የሚወስዱትን እርምጃ እንደሚደግፍ ለማሳወቅ ይወዳል።
    መላው ኢትዮጵያዊያንም ሀገራችን ሰላም እንዳትሆን፤ ዜጎችም እርስ በእርስ እየተጠራጠሩና እየተጠቃቁ እንዲኖሩ፤ በዚህም መሃል በወገን ደም ለመነገድ የሚጥሩ ሀይሎችን ሴራ ተረድቶ፤ በዘመን የተሳሰረ ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነትን ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ በማጠናከር የክፉዎችን ሴራ እንደምታከሽፉት አስተዳደራችን በፅኑ ያምናል፡፡
    በመጨረሻም በንፁሃን ላይ በደረሰው የህይወት ህልፈት እንደድሬዳዋ አስተዳደርና ነዋሪዎች እንዲሁም የፓርቲ ፅ/ቤት ሀዘናችንን ዳግም እየገለፅን፤ ለመላው ኢትዮጵያዊያን መፅናናትን እንመኛለን፡፡
    የድሬዳዋ አስተዳደር
    እና
    የድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ፅ/ቤት
    ጥቅምት 23/2013 ዓ.ም.
    ድሬዳዋ/ኢትዮጵያ