የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች አለም አቀፍ ማህበር በድሬዳዋ ከተማ ድጋፍ አደረገ::

    የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች አለም አቀፍ ማህበር በድሬዳዋ ከተማ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ከ250 ሺ ብር በላይ የሚገመት የትምህርት መርጃ ቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ፡፡
    በድጋፉ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጀዋር እንደገለፁት በአስተዳደሩ ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ መስኮች እየተደረገ የሚገኘው የመተጋገዝ ስራ የድሬዳዋን የመቻቻልና የፍቅር ከተማ ስያሜ የሚያጎላ ተግባር መሆኑን እንዲሁም ምሳሌአዊ ተግባር መሆኑን ገልፀው በውጭ የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች እያከናወኑ ለሚገኘው መልካም ስራ በአስተዳደሩ ስም አመስግነዋል፡፡
    የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ከድር ጀዋር ከዚህም ጋር በማያያዝ የመንደርና የሰፈር ፖለቲካ የትም አያደርስም በማለት፤ ይህ አይነቱ በጎ ተግባር ተምሳሌትነታችንን የምንመልስበትና የምናስተካክልበት በመሆኑ የህግ የበላይነት አንደሚረጋገጥ በዚሁ አጋጣሚ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ ብለዋል፡፡
    የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች አለም አቀፍ ማህበር የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ አንበስ እንግዳ እንደገለፁት ማህበሩ ከባህር ማዶ ሀገራት ከሚገኙ አባላቱ ከሚያሰባስበው ድጋፍ ላለፉት 2 አመታት ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር አውስተው ቀደም ሲል ካበረከተው የ4 መቶ ሺ ብር ድጋፍ ባሻገር አሁን ያደረጉት ድጋፍ ከ250 ሺ ብር በላይ በሆነ ወጪ ለ1 መቶ ተማሪዎች የትምህርት መርጃ ቁሳቁስና ለእያንዳንዳቸው የሺህ ብር ጥሬ ገንዘብ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ማህበሩ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ መሳሪያ ከውጭ በማስገባት ስጦታ አበርክተዋል ፡፡