አቢቹ አባ መላ ABICHU ABBAA MALAA የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፤ በጦር ግንባር ተሰልፈው ሰራዊቱን በመምራት ላስመዘገቡት ድል “አብቹ አባ ቢያ” የሚል የገዳ ስርዓት የጀግንነት ስያሜ መስጠቱን አስታውቋል።

    ህብረቱ ዛሬ ባካሄደው ጉባዔ፤ በከረዩ አባ ገዳ ላይ ጠላት የፈፀመውን ግድያ በጽኑ በማውገዝ፤ ከአሸባሪው ህወሃት ጋር ህብረት የፈጠረ ማንኛውም አካል የኦሮሞ ጠላት እንደሆነ መወሰኑን አስታውቋል።
    የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ፀሐፊና የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ፤ የኦሮሞ ህዝብ እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም ከሌሎች ወንድም የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ለሀገር አንድነት የላቀ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልፀው፤ “ጠላት ‘ሀገር ፈረሰች’ ብሎ ሲጠብቅ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር ሰራዊቱን በአካል ተገኝተው በመምራት፤ ህዝብን ከስጋት ከማላቀቅ ባለፈ የሀገሪቷን ህልውና ያረጋገጠ ድል እንዲመዘገብ አድርገዋል” ነው ያሉት።
    የመጫ ኦሮሞ አባ ገዳ እና የህብረቱ አባል አባገዳ ወርቅነህ ተሬሳ በበኩላቸው፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት የተመዘገበው ድል የመላው ኢትዮጵያዊያን ድል መሆኑን አመልክተው፤ “ድሉ የውስጥና የውጭ ጠላት በሀገራችን ላይ የሸረቡትን ሴራ የበጣጠሰ ከመሆኑም ባለፈ፤ የተጀመረውን ዘመቻ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ትልቅ ወኔ የሰነቀ ነው” ብለዋል።
    ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፤ ሀገርን ለማዳን ከቤተ መንግስት ወጥተው በግንባር ጦሩን በመምራት ላስመዘገቡት ድልና ጀግንነት፤ የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት አድናቆትና ምስጋና መቸሩን ገልጸው፤ “ህብረቱ በኦሮሞ የጀግና ስያሜ ሞጋሳ መሰረት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘አብቹ አባ ቢያ’ የሚል የገዳ ስያሜ ሰጥቷል” ሲሉ ይፋ አድርገዋል።
    አክለውም ”ከአሸባሪው ህወሃት ጋር ህብረት የፈጠረው ሸኔ የኦሮሞ ጠላት ነው” ሲሉም የህብረቱን አቋም የገለፁት አባ ገዳ ወርቅነህ፤ ከኦሮሞ ህዝብ አንድነትና ፍላጎት በተፃረረ መልኩ፤ ከጠላት ጋር የተሰለፉ የሸኔ ታጣቂዎች እጃቸውን ለመንግስትና ለአባ ገዳዎች እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
    የአርፈን ቀሎ አባገዳ ሸምል አህመድ በበኩላቸው “በአሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ እኩይ ሴራ ተታለው ጫካ የገቡ የኦሮሞ ልጆች ካሉ ተመልሰው ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሆን ጠላትን ማጽዳት አለባቸው” ብለዋል።
    “ከአሸባሪው ህወሃት ጋር ጥምረት የፈጠረ ማንኛውም አካል የኦሮሞ ጠላት ነው፤ የኦሮሞ ህዝብ ለዘመናት የሞተለትን ዓላማ በመዘንጋት ከጠላት ጋር ማበር ውርደት ነው” ያሉት ደግሞ የኦዳ ሮባ ሲኮ መንዶ አባገዳ አሊይ ሙሐመድ ሱሩር ናቸው።
    “በከረዩ አባ ገዳ ላይ የተፈፀመው ግድያ የኦሮሞን ህዝብ ለማዋረድ ያለመ የጠላት ተግባር በመሆኑ ፍትህ እንፈልጋለን” ብለዋል። ግድያውን በማውገዝ፤ ወንጀሉን የፈፀሙ አካላት በአፋጣኝ ለህግ መቅረብ እንዳለባቸው ያስገነዘቡት፤ የቦረና አባገዳ ኩራ ጃርሶ ናቸው ሲል ኢዜአ ዘግቧል።