የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮና የቀበሌ ኮሚኒኬሽን ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተጠቆመ::

    የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮና በቀበሌ ደረጃ ያሉ የኮሚኒኬሽን ዘርፍ ባለድርሻ አካላት የግንኙነት አግባብና ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በሁለቱ ባለድርሻ አካላት መካከል በተደረገው የምክክር መድረክ ተገልጿል፡፡
    በምክክር መድረኩ ቢሮው ያደረገው የመስክ ጉብኝት ሪፖርት የቀረበ ሲሆን የሰው ሃይልና የግብዓት እጥረት፣ የግንኙነት አግባብ መላላት፣የስራ አፈፃፀምን ሪፖርት በወቅቱ አለማቅረብ መስተዋሉን ሪፖርቱን ያቀረቡት የቢሮው ባለሙያና የመስክ ጉብኝቱ ቡድን አባል አቶ ታሪኩ ዘውዱ ተናግረዋል፡፡
    የውይይት መድረኩ ተሳታፊ የኮሙዩኒኬሽን ማስተባበሪያዎች ባለሙያዎችና አመራሮች ስራዎቻቸውን በውጤታማነት ለመስራት የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ለዚህም ምላሽ የሰጡት በቢሮው የጥናትና ምርምር ቡድን መሪ አቶ የማነ ስንታየሁ የስልጠና ፍላጎትን መሰረት በማድረግ በቀጣይ የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥ ገልፀዋል፡፡
    በመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሙአዝ አሊ ተቋማቸው ቀበሌዎችን እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ገልጸው ድሬ ጋዜጣን ጨምሮ በኤሌክትሮኒክስ መረጃ መስጫ መንገዶችም ስራዎቻቸውን ለማገዝና ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በሚደረገው ሂደት ተቋሙ የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡