በድሬደዋ የመስቀል ደመራ በአል በህዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ በድምቀት ተከብሯል ።
በበአሉ ላይ ተገኝተው በክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት ለሚከበረው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በማይዳሰስ ቅርስነት ለተመዘገበው የመስቀል ደመራ በዓል እንኳን በሠላም አደረሳችሁ! በማለት መልዕት ያስተላለፉት የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ የመስቀል ደመራ በዓል የሀገራችንን የኃይማኖት ብዝሀነት ድንቅ ዕሴት ለመላው ህዝባችን እና ለውጭው ዓለም ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለዘለቄታው የሚያስጠብቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
ህዝበ ክርስቲያኑ በተለይ ወጣቱ ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ የሠላም፣ የአንድነት እና የመቻቻል ኃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊቱ ሳይጓደል ከሌሎች እህት እና ወንድም ኃይማኖት ተከታዮች ጋር በጋራ በድምቀት በማክበር የድርሻውን መወጣት እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡
የመስቀል ደመራ በዓል ኃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓት ህዝበ ክርስቲያኑ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ወድሞቹ ጋር በአብሮነት በአደባባይ የሚያከብረው በዓል መሆኑን አውስተው በአሉ በቀጣይ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቁበት ከመሆኑም በተጨማሪ የአስተዳደራችንምሆነ የሀገራችን መንግስት የጀመረውን ለውጥ እና የብልጽግና ጉዞ በጥልቀት በማስቀጠል ነዋሪው የሚያነሳቸውን የሠላም፣ የልማት፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እንዲሁም የሥርዓታችን ብቻ ሳይሆን ለህልውናችን አደጋ የሆኑትን ታሪካዊ ጠላቶቻችን፣ተላላኪዎች፣ ፀረ-ሠላም ኃይሎችና ተባባሪዎቻቸውን ዕኩይ ሴራ ለመመከት በከፍተኛ ህዝባዊ ተሳትፎ በፅናት ታግለን ከምንጩ ለማድረቅ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅት መሆኑ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
አስተዳደራችን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መናሐሪያና ትንሿ ኢትዮጵያ ስትሆን ነዋሪዋም በመቻቻልና በመፈቃቀር በሠላም መኖር ከመቻሉም በላይ የኃይማኖት ብዝሃነት፣ የመከባበር ማህበራዊ ዕሴቶቹን አስጠብቆ ለጋራ መግባባት፣ ሠላም፣ ልማትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንዲሁም ለብልጽግና ጉዞ ስኬት በማዋል እያበረከተ ያለውን ህያው አስተዋፅኦ ታላቅ አክብሮት የሚቸረው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም አዲሱ ዘመን የሀገራችን ከፍታ ይሆን ዘንድ የብልፅግና ጉዞን በላቀ ደረጃ ለማስፈፀም ባለን አቅም ሁሉ ልንረባረብ ይገባል ያሉ ሲሆን በዓሉ የሠላም፣ የደስታና የስኬት እንዲሁም የተቸገሩትን የምንረዳበት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡
በዳግማዊ ፍቃዱ
ፎቶ፦በሰላም አበበ


