የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ለ120 ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ለአንድ መቶ ሀያ ተማሪዎች ብዕር፣ ደብተር፣ እንዲሁም ዩኒፎርም አሰፍቶ ለትምህርት ቢሮ አስረክቧል፡፡ በድጋፍ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር በማድረግ ድጋፉን የሰጡት የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ አብዲ ሙክታር ናቸው፡፡
አቶ አብዲ የቢሮ ሰራተኛው ተርፎት ሳይሆን ካለው ላይ ለአቅመ ደካማ ተማሪዎች የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ በትምህርት መስኩ ላይ ከዚህ የበለጠ ድጋፍ ለማድረግ ማሰባቸውን ተናግረዋል፡፡
ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎች በርትተው ተምረው እራሳቸውን፣ አካባቢያቸውን እንዲሁም ሀገራቸውን መለወጥ እንደሚኖርባቸው አቶ አብዲ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ትምህርት ቢሮ ይህን ድጋፍ ዛሬ ተረክቦ በአግባቡ ለሚመለከታቸው ተማሪዎች እንደሚያደርስ ተስፋ እያደረግን፤ በስነ ምግባር የመቅረፅ ሀላፊነት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም አቶ አብዲ ለአምስት ትምህርት ቤቶች የተደረገው ድጋፍ በብር ሲሰላ ከሁለት መቶ ሺህ ብር በላይ እንደሚሆን ጠቅሰዋል፡፡
ሌላው ድጋፉን የተቀበሉት የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ሀላፊ የሆኑት አቡበከር አብዶሽ ናቸው፡፡ እንደ አቶ አቡበክ ገለፃ ከሆነ የተማረ የሰው ሀይል ለማፍራት የትምህርት ሴክተሩን መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የመግዛት አቅም የሌላቸውን የተቸገሩ ወገኖቻችንን በመደገፍ የጥንቱን የመደጋገፍ ባህላችንን ማስቀጠል ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
የተማረ የሰው ሀይል ማፍራት የትምህርት ሴክተሩ የተሰጠን ሀላፊነት ቢሆንም ከሌሎች ተቋሞች ጋር በጋራ በመሆን ለትምህርት መማሪያ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን መግዛት ለማይችሉ ለአቅመ ደካሞች መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አንድ ተማሪ ያለትምህርት ቁሳቁስ ከትምህርት እንዳይርቅ ተብሎ፤ በአገር አቀፍ የተጀመረው ንቅናቄን ዛሬ የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ በሰራተኛውና አመራሩ ተነሳሽነት ለአምስት ትምህርት ቤት የተደረገውን ድጋፍ መቀበላቸውን አቶ አቡበከር ገልፀዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ዛሬ ብቻ አይደለም ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጉን አቶ አቡበከር ተናግረዋል፡፡ ለተደረገው ድጋፍ አቶ አቡበከር በቢሮ ማኔጅመንት እና በራሳቸው ስም አመስግነዋል፡፡
በበድሉ ሀይሌ
ፎቶ፡- ሰላም አበበ