በሀገርአቀፍ ደረጃ በህግ ጥናቶችና ምርምሮች ላይ የተካሄደዉ የምክክር መድረክ ተጠናቀቀ ::

    የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ እና የኢፌድሪ የህግ ስልጠና እና ምርምር ኢኒስቲትዩት በጋራ አዘጋጅነት ከተለያዩ የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የህግ ትምህርት ክፍሎች እና የህግ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት በህግ ጥናቶችና ምርምሮች ላይ አተኩሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው የምክክር መድረክ ተጠናቀቀ ፡፡
    በዚህ የምክክር መድረክ ያነጋገርናቸዉ የኢፌድሪ የፍትህና ህግ ስልጠና እና ምርምር ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ምትኩ ጊዶ እንደገለፁት የመድረኩ ዓላማ በሀገራችን ከህግና ፍትህ ተደራሽነት ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ ችግሮች ከሚፈቱባቸዉ መንገዶች አንዱ የህግ ስልጠና እና ምርምር መሆኑን አብራርተው ሁሉም የመድረኩ ተሳታፊዎች ጥናትና ምርምሮቹን እንደግብዓት በመጠቀም በሀገራችን የፍትህ ስርዓቱን ዘመናዊ፣ተደራሽ፣ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የበኩሉን ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
    የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የአካዳሚክ ጉዳዮች ሀላፊ የሆኑት ዶ.ር መገርሳ ቃሲም በበኩላቸው በሀገራችን ብሎም በተለያዩ የዓለም ሀገራት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋሉ ግጭቶችን ለመቀነስ ብሎም ለማስቆም የህግ ጥናትና ምርምሮች ፋይዳ የጎላ በመሆኑን ገልፀዋል፡፡
    የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ኮሌጅ ዲን የሆኑት አቶ አመንቴ አበራ በምክክር መድረኩ ላይ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ እና በተለያዩ የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የህግ ትምህርት ክፍሎች የተካሄዱ 10 የጥናትና ምርምሮች ላይ ውይይት መካሄዱንና ጥናትና ምርምሮቹ የሰብዓዊ መብቶች ላይ ማተኮራቸዉ በሀገራችን የፍትህ ተደራሽነት ለማሻሻል የጎላ ድርሻ ያለው መሆኑን አብራርተዋል፡፡