በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን እቅስቃሴ መነሻ በማድረግ የድሬዳዋ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ አደረጃጀት<<ምክንያታዊ ወጣት እንፍጠር>>በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው የውይይት መድረክ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአስተዳደሩ ም/ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር እንደተናገሩት ወጣቱ መሰረታቸው ያልታወቁ መረጃዎችን ሳይከተል እንዲሁም ሁኔታዎችን ሲደግፍም ሆነ ሲቃወም ምክንያታዊ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የምክንያታዊ ወጣቶች ንግግርና ሙግት በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን ሰነድ ያቀረቡት አቶ አለማየሁ ሰይፉ ወጣቱ የሀገረ መንግስት ግንባታ ምንነት፣ የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደትና ት/ት የሚወሰድባቸው ጉዳዮች፣ የሌሎች ሀገራት የሀገረ መንግስት ግንባታ ልምዶች፣ የሀገረ መንግስት ግንባታን እውን ማድረግ ይቻል ዘንድ የአገራችን የፌደራል ስርዓት ያስገኛቸው ስኬትና የወጣቱ ሚናና የሚቀስሟቸው ልምዶች የሚሉ ነጥቦችን ዘርዝረው አቅርበዋል።
ዜጎች በእኩልነት ተንቀሳቅሰውና ሰርተው ህይወታቸውን የሚመሩባት፣ ሰላምና ብልጽግና የተረጋገጠባትን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ይቻል ዘንድ ሀገረ መንግስቱ ሊቆምባቸው የሚገባ ምሰሶዎችና ሌሎች ሀሳቦች በተሳታፊዎች ተነስተው በመድረክ መሪዎች ሰፊ ማብራሪያ በመስጠት በቀጣይ ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ተመላክተዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ ወጣቶችም በሰጡት አስተያየት ሀገር በመገንባት ሂደት ውስጥ የወጣቱ ተሳትፎው ጉልህ እንዲሆን ስለሚጠበቅ የተዘጋጀው ውይይት ለወጣቱ ሚዛናዊ የሆነ አስተሳሰብ እንዲያጎለብት ያግዘዋል ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዋቹ አያይዘውም ቀደም ሲል ወጣቱ ለሚያናሳቸውና ለሚያራምዳቸው የትኛውም አቋሞች አሳማኝና አመክንዮታዊ የሆነ ሀሳብ ባለማቅረብና በስሜት በመገፋፋት ለተለያዩ የጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ ሆኖ የቆየ መሆኑን በመጥቀስ አሁን የተፈጠረው መድረክ ሲስተዋል የነበረውን የአመለካከትና የአስተሳሰብ ክፍተት ለመቅረፍ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡ በተያያዘም በሀገር ደረጃ በሚካሄደው 6ተኛው ሀገራዊ ምርጫም ለሀገሩ ዕድገት በትክክል የሚበጀውን ፓርቲ በመለየት በምክንያት ለመደገፍም ሆነ ሌላውን ለመቃወም የሚችል የተስተካከለ አስተሳሰብ እንዲኖረውም ያግዛል ብለዋል ፡፡ በመጨረሻም ምክንያታዊ ወጣት የመፍጠር እንቅስቃሴው በአንድ ቀን የሚሳካ ባለመሆኑ በቀጣይ ተመሳሳይ ስራዎች በተለያዩ አደረጃጀቶች መስራት ተገቢ እንደሆነና ወጣቱ ይህን ስራ ሊያግዝ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ ከአስተዳደሩ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን ወጣቶች መሳተፍ ችለዋል።


