የዘንድሮ የጥምቀት በአል ፍጹም ሰላማዊ እንዲሆን ከበአሉ ቀን ቀደም ብሎ ፖሊስ ቅድመ ዝግጅቶችን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በዚህም ከተለያዩ የእምነት አባቶች፤ከወጣቶች፤ከህብረተሰቡ የተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በዚህም ሃይማኖታዊ ይዘቱን ሳይለቅ በአሉ እንዲከበር ጥሩ መግባባት ላይ መደረሱን የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ሃላፊ ም/ኮሚሽነር ጉሌድ ድርዬ ገልጸዋል
የጥምቀት በአል በድሬዳዋ ከተማ ሲከበር ሃይማኖታዊ ስርአቱን ይዞ እንዲከበር ለማስቻል የእምነቱ ተከታዬች እና የከተማው ነዋሪ ከፍተኛ ተግባር መፈጸም እንዳለበት የገለጹት ም/ኮሚሽነር ጉሌድ ከዚህ ውጪ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከሃይማኖታዊ ስርአቱም ሆነ ከህግ አግባብ ውጪ በመሆናቸው መላው የአስተዳደሩ ነዋሪዎች ከዚህ ህገ-ወጥ ተግባር እራሳቸውን በማራቅ ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በአላትን አስታኮ ሃይማኖታዊ ስርአትን ለማወክ መሞከር አይቻልም ያሉት ም/ኮሚሽነር ጉሌድ የፖለቲካ ይዘት ያላቸውን ቲሸርቶች መልበስ፤ከፌደራሉ ባንዲራ ውጪ መጠቀም ፤በተለያዩ ቦታዎች ላይ ቀለም መቀባት፤እንዲሁም ርችት መተኮስ የተከለከሉ ተግባራት ሲሆኑ በዚህ ህገ-ወጥ ተግባር ላይ ለመሳተፍ የሚሞክር ማንኛውንም ግለሰብ ላይ የማያዳግም ተገቢው የህግ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ም/ኮሚሽነር ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት አመታት በአላትን ተከትሎ የተፈጸሙ ህገ-ወጥ ተግባራት የአስተዳደሩን ነዋሪ ያሳዘነ ፤በሃገር አቀፍ ደረጃም የከተማችንን መልካም ገጽታ ያበላሸ መሆኑን ያወሱት ም/ኮሚሽነር ጉሌድ ይሄ ተግባር ዘንድሮ በፍጹም እንደማይደገም አስታውቀዋል፡፡
በዘንድሮ የጥምቀት በአል አከባበር ቦታዎች ላይ ሲመጣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣውን የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመከለከል የፊት መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ ግዴታ ሲሆን ፖሊስ ለሚያደርገው አካላዊ ፍተሻም ትበብር ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ከፖሊስ አካላት ብቻ የሚሰጡ ተእዛዛትን ማክበር ይገባል ያሉት ም/ኮሚሽነር ጉሌድ ከዚህ ውጪ የሚደረጉ ህገ-ወጥ ተግባራት አይፈቀዱምም፤ አይቻልምም ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የጥምቀት በአል የሰላም የደስታ እንዲሁን መልካም ምኞታቸውን ም/ኮሚሽነር ጉሌድ ገልጸዋል፡፡
ምንጭ ድሬ ፖሊስ


