ሀገራችን ተገዳ የገባችበት የህልውና ዘመቻ ጦርነት ለመቀልበስ እንዲሁም የሀገራችንን ሰላም ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ ከድሬዳዋ የዘመቱ አርሶና አርብቶ አደሮች አሉ ። የነዚህንም ዘማቾች እርሻ ከዘማች ቤተሰቦች ጋር በጋራ በመሆን የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰቡ ስራ በዛሬው እለት በቢዮ አዋሌ ክላስተር አዳዳ ቀበሌ ገ/ማኅበር የተጀመረ ሲሆን በዚሁም ስራ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀርን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ፣ የግልና የመንግስት ትምህርት ቤት ተማሪዎችና መምህራን ተሳታፊ ሆነዋል ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በተላለፈው ጥሪ መሰረት የዘማች ቤተሰቦችን በማገዝና የደረሱ ሰብሎችን በማጨድና በማገዝ ከዘማች ቤተሰቦች ጎን መሆናቸውን ያሳዩበት እንደሆነ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ተናግረው አሁን ላይ የተጀመረው ስራም በቀጣይ በእርሻዎቹ ላይ የደረሱ ሰብሎች ታጭደው እስቂያልቁ ድረስ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው አቶ ከድር ጁሀር በእለቱ የተናገሩት ።
በድሬዳዋ አስተዳደር በ2013 \ 14 የምርት ዘመን 14 ሺህ 445 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ 14 ሺህ 671 ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን የድሬዳዋ አስተዳደር የግብርና ማእድንና ኢነርጂ ቢሮ ሀላፊ የሆኑት አቶ ኑረዲን አብደላ ተናግረው ከ 280 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ እንደታቀደና ይህም እንዲሳካ በተለይም ከግብአት አቅርቦት ፣ አርሶ አደሩን ከማደራጀትና ከማስተማር እንዲሁም ኤክስቴንሽን አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ዘርፈ-ቡዙ ስራዎች መሰራታቸውን አቶ ኑረዲን ተናግረዋል ።


