አንድ ሚሊየን የሚገመት አልባሳትና ደረቅ ምግቦች በጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ተሰጠ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የድሬዳዋ ሀገረ ስብከትና ምዕመናን በጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት አልባሳትና ደረቅ ምግቦች ድጋፍ አደረገች ፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከዲር ጁሃር መሀመድ ድጋፉን ተረክበዋል ፡፡
የአስተዳደሩ ከንቲባ ከዲር ጁሃር ድጋፉን ከተረከቡ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት የድሬዳዋ ሀገረ ስብከትና ምዕመኑ በጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖች ለሰጠው ፈጣን ምላሽ በራሳቸውና በአስተዳደሩ ስም አመስግነው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ የታየው መነሳሳት በድሬዳዋ ልማትና ጽዳት ላይም እንዲደገም ጥሪ አቅርበዋል ፡፡ አስተዳደሩና የዕመነት ተቋማት በሀገር ጉዳይና በልማት ስራዎች ዙርያ በጋራ መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹት ከንቲባው የድሬዳዋ ሰላምና ጸጥታ እንዲጠበቅ በየቤተክርስቲያኑ መልዕክት እንዲተላለፍ ጥሪ አስተላልፈዋል ፡፡
የድሬዳዋ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በረክክቡ ስነስርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የእናት ጡት ነካሽ የሆነው ጁንታ ኢትዮጵያን ለማዋረድ ከውስጥና ከውጭ በከፈተብን ጦርነት የኃይማኖት ተቋማትን አርክሷል ፣ ወገኖቻችን እንዲራቡና እንዲታረዙ አድረጓል ፤ ወገኖቻችንን ገሏል ደፍሯል ፡፡ ይህንን ሁኔታ ለመቀልበስ የሁሉም ዕምነት ተቋማት የራሳቸውን ኃላፊነት ወስደው እየሰሩ ያሉት ስራ ሊበረታታና ሊቀጥል የሚገባው ነው ብለዋል ፡፡


