የኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ የማህበራዊ ጤና መድህን ስርአትን ለማስፈጸም በሚኒስተሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 191/2003 አንቀጽ 9 በተሰጠው ስልጣን መሰረት መመሪያ አውጥቶ ደንቡን ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ይህን ደንብና መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ የድሬደዋ አስተዳደር የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ፍትሀዊነትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ትግበራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡የፕሮግራሙን መልካም አፈጻጸም ለማስቀጠል አመራሩንና መላ ህዝቡን አስተባብሮ በመምራት እና የጤና መድህን ሽፋንን በ2014 በጀት አመት በስፋት ለማስፋፋት የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ለማሳደግ ያለመ የንቅናቄ መድረክ የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ በዛሬው እለት የምዝገባና የዕድሳት ስራ ውጤታማ ለማደረግ የሚያስችል ሰነድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄዷል፡፡
በውይይት መድረኩ የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር እንደተናገሩት የጤና መድህን በአስተዳደሩ ለማረጋገጥ የአባልነትን ምጣኔ ለመጨመርና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተገኘውን መልካም አፈጻጸም ለመስቀጠል ከታህሳስ 15 እስከ የካቲት 30 ድረስ አመራሩ እና መላ ህዝቡን አስተባብሮ በመምራት ንቅናቄው የተሳካ እንዲሆን ከከፍተኛ እስከ ታችኛው አመራር፤ የጤና ባለሞያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላትና የሀይማኖት ተቋማት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የጤና መድን ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሀርቢ ቡህ ለመድረኩ ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልእክት በምርጫ ተወዳድረን ህዝቡ እኛን ሲመርጠን የገባንለትን ቃል ተግባራዊ እንድናደርግ በመሆኑ የጤና አገልግሎቱ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ማድረግ ከሁላችንም ስለሚጠበቅ ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል ብለዋል፡፡
የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ በበኩላቸው በ 2013 በጀት አመት 21 ሺህ የሚሆኑ አባላት መኖራቸውን ጠቁመው በዚህም አፈፃፀም የተሻለ አፈፃም ካላቸው ክልሎች ድሬዳዋ አንዷ በመሆኗ ውጤታማ አድርጎናል በማለት ይህ አገልግሎት የሚሰጠው በድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን እስከ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሪፈር ይዘው ሄደው አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ ብለዋል፡፡
ኃላፊዋ ከዚህም ጋር አያይዘው እንደተናገሩት የምዝገባና የመታወቂያ እድሳት ጊዜው ከታህሳስ 15 እስከ የካቲት 30 ብቻ በመሆኑ ከዚህ ቀን ውጪ የመጡ ምዝገባም ሆነ እድሳት የማይኖር መሆኑን በመረዳት ጊዜው ሳያልፍ እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡


