በሴቶችና ህፃናት ላይ በጁንታው ህወሃት ቡድን እየደረሰ የሚገኘውን ጥቃት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተቃውሞ ድምፃችሁን ለማሰማት ከተለያዩ የሴት አደረጃጀቶች፣ሴት ተማሪዎችና የመንግስት ሰራተኞች ለተውጣጣችሁ የእዚህ የንቅናቄ ሰልፍ ተሳታፊዎች በቅድሚያ የከበረ ሰላምታዬን አቀርባለሁ፡፡
ሴቶች የአንድ አገር የማዕዘን ድንጋይ ናቸው፡፡ ያለ ሴቶች ሁለንተናዊ ድጋፍ የአገርን ልማትና ዕድገት ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ በመሆኑም ለሴቶች ደኅንነትና ህልውና መረጋገጥ እንዲሁም የሴቶችን ተሳትፎ ለማስፈንና ለማሳደግ የአንድ ሀገር ብሎም የአንድ መንግስት ድርሻ ከፍ ያለ ነው፡፡
ዕውነታው ይሄ ቢሆንም የአገራችን ጠላት መሆኑን በአደባባይ ያወጀው ጁንታውና አሸባሪው የህወሃት ቡድን በስልጣን ላይ በቆየባቸው 27 ዓመታት የሴቶችን መብትና ደኅንነት ከማረጋገጥ ይልቅ በሴቶች ላይ ጭቆና ሲያሳድር ቆይቷል፡፡ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎአቸውንም ሲገድብ ኖሯል፡፡
የጀግናው የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የክህደት በትሩን በመሰንዘር የመንግስትን ሆደ ሰፊነት ከንቀት በመቁጠር ጆሮ ዳባ ልበስ ያለው ይህ አሸባሪ ቡድን ለረጅም አመታት ሲመራት ለነበራት አገርና ህዝቦቿ ደንታ የሌለው ይልቁንም ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ለርካሽ የፖለቲካ ፍጆታውና ሀብት ማካበቻነት ሲጠቀምባቸው የኖረ የሚመራትን ሀገር እንኳን ስም ለመጥራት የሚፀየፍ የአገር ፍቅር የሌለው መሆኑን በገሀድ አሳይቷል፡፡ለዚህም በተለያዩ ጊዜያት አላስፈላጊ የራሱን ሰራዊት በማደራጀት፣የሚቃወሙትን ዜጎች በገፍ በማሰር፣ ወከባና ማስፈራራት በመፍጠር፣ህገወጥ ግንኙነቶችን ከውጪ መንግስታትና አካላት ጋር በማድረግ ኢትዮጵያን እንዴት እንደሚያፈርስ ሲያሴር መቆየቱና አሁንም ይህን ቅዠት የሆነ ህልሙን ዕውን ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ አብይ ማሳያ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቢሮ በጋራ ባጠኑት ጥናት በርካታ ሴቶች መደፈራቸው ተረጋግጧል፡፡
ከምንም በላይ ሴቶች በዚህ አሸባሪና ከሀዲ ቡድን ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፡፡ ሰብዓዊ መብቶቻቸውን ከመገፈፍ ባለፈ ለመደፈርና ለተለያዩ ጥቃቶች ተዳርገዋል፡፡በዚህም ለተለያዩ የስነልቦና ጫናዎች ተጋላጭ ሆነዋል፡፡ከመኖሪያ አካባቢያቸው በመፈናቀልም በርካታ ማህበራዊ ችግሮችን ተጋፍጠዋል፡፡ለተጨማሪ ልፋቶችና የጤና ችግሮች ከመጋለጣቸው ባሻገር ለአስከፊ ስቃይና ሞት ይህ አሸባሪ ቡድን አሳልፎ ሰጥቷቸዋል፡፡
ይህን ዕኩይ ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያውያን ጫንቃ ላይ ለማላቀቅ የሴቶች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን የአሸባሪውን ቡድን ለማስወገድ የሚያደርገውን ተጋድሎ ሰራዊቱን በደጀንነት በመደገፍ፣ለዘማች ቤተሰቦች እንክብካቤ በማድረግ የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ህግ የማስከበርና የህልውናው ዘመቻ እስኪጠናቀቅ ድረስ እደረጋችሁ ያላችሁትን አስተዋጽኦ አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡
ይህን መሰል የንቅናቄ ሰልፍ የሴቶችና የህፃናትን ሰቆቃ ለአለምአቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ በማድረግና ተፅዕኖ በማሳደር ረገድ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡አሸባሪው የህወሃት ቡድን በሴቶችና ህፃናት ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት ለአለምአቀፉ ማህበረሰብ ለማሰማት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
በመጨረሻም ይህን የንቅናቄ ሰልፍ በማስተባበርና በተለያየ መልኩ አስተዋጽኦ ላደረጋችሁ አካላት ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
የኛ ሰላም ይስፈን በሴቶችና ህፃናት የሚደርስ ጥቃት ይቁም!


