የ17ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ የተሰጠ መግለጫ

    የተከበራችሁ መላው የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች እና የሀገራችን ዜጎች “ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ቃል በታላቅ ድምቀት ለምናከብረው 17ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል እንኳን በሠላም አደረሳችሁ! አደረሰን!

    በመቀጠልም ሕብረ ብሔራዊ ብዝሃነት ባለባቸው እና ሕገ-መንግሥታዊ ዕውቅና በሰጡ ሀገራት የተዘረጋውን የፌደራል ሥርዓትን ስንመለከት ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዓላማዎች እንደተጠበቁ ሆኖ በዋናነት ከማንነት ጋር ተያይዘው ለሚነሱ በርካታ ጥያቄዎች የተሻለ አማራጭ መፍትሔ በመስጣት የግዛት አንድነታቸውን እና ሉዓላዊነታቸውን ማስጠበቅ እንደ ቻሉ እናስተውላለን፡፡

    ሀገራችን ኢትዮጵያም የባህል፣ ወግ፣ ቋንቋ፣ ኃይማኖት ወ.ዘ.ተ ብዝሃነት ባለቤት እንደመሆኗ ብዝሃነቷ ለረጅም ዓመታት በተገቢው መንገድ ባለመስተናገዱና ሕጋዊ ዕውቅና ተነፍጎት በመቆየቱ ምክንያት በዋናነት የብሔር እና ማንነት እንዲሁም አያሌ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች የፌዴራላዊ ብሔረ መንግስት ግንባታ አስተሳሰብን መሠረት አድርገው ከ1960ዎቹ ወዲህ በሀገራችን ከፍተኛ የህዝባዊ ንቅናቄ ታሪካችን አካል እንደነበር ይታወሳል፡፡

    ስለሆነም ለብዝሃነት በግልፅ ሕገ-መንግስታዊ ዕውቅና መስጠት የተቻለው የኢፌዲሪ ሕገ- መንግሥት ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ከመፅደቁ ጋር ተያይዞ ሲሆን ራስን በራስ የማስተዳደር፣ በቋንቋ የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋን የማሳደግ፣ ባህልን የመግለፅ፣ የማዳበርና ማስፋፋት፣ ታሪክን የመንከባከብ እና የመሳሰሉትን መብቶችን ለማረጋገጥና ለማክበር ታስቦ እንዲሁም ሕገ-መንግሥቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትና ምንጭ መሆናቸውን ከግምት በማስገባት ሕገ-መንግሥቱ የፀደቀበትን ህዳር 29 ቀን “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን” ተብሎ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሚያዚያ 21 ቀን 1998 ዓ.ም ተወስኖ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ መድረክ እየፈጠሩ ባህላቸውን፣ ወጋቸውን፣ የአኗኗር ዘይቤያቸውን፣ ልምዳቸውንና መሠል ቁምነገሮችን በማጋራት በድምቀት ሲያከብሩ ቆይተዋል፡፡

    ዘንድሮም ለ17ኛ ጊዜ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት “ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን በዓል ምክንያት በማድረግ በአስተዳደራችን በልዩ ልዩ ህዘዝባዊ ሁነቶች በጋራና በድምቀት ስናከብር ሕብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆን የምናደርገው ሁለነተናዊ ጥረት ለሀገራችን ኢትዮጵያ የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን ሁሉን ማሰባሰብ እንዲሁም ሀገርን አንድ አድርጎ፣ ሠላሟን እና ሉዓላዊነቷን አስጠብቆ የማስቀጠል የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ሁላችንም የሚጠበቅብንን የዜግነት ኃላፊነታችንን ለመወጣት ከመቼውም ጊዜ በላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባን በድሬዳዋ አስተዳደር ስም ለማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡

    በመጨረሻም በዓሉን ስናከብር የብሔር ማንነት ብቻውን ጎልቶ እንዲታይ በማድረግ ሀገራዊ ማንነትን እና አንድነትን ከሚያደበዝዙ እንዲሁም የዘላቂ ሠላም ግንባታችንን ሊያዘገዩ ብሎም ሊያቀጭጩ የሚችሉ አስተሳሰቦችን ከማራመድ ተቆጥበን ሕብረ ብሔራዊ አንድነታችንን አጠናክረን በማስቀጠል በአስተዳደሩን ብሎም በሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብዝሀነት፣ አብሮነት፣ ወንድማማችነት፣ ፍቅር እና ፍጹም አንድነት እንዲጎለብት እንዲሁም ለአስተዳደራችንም ሆነ ሀገረችን ማህበራዊ፣ ኢኮሚያዊ ብልጽግ እና ዘላቂ ሠላም ግንባታ ልንጠቀምበት እንደሚገባ አደራ እያልኩ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ!

    ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቷን አብዝቶ ይባርከ!

    ክቡር አቶ ከድር ጁሀር ኢብራሂም
    የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ

    ህዳር 16 ቀን 2015 ዓ.ም
    ድሬዳዋ