17ኛው የብሄር ብሄረሰቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ ” ፌደራሊዝም፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነትና ህገ-መንግስታዊ ” በሚል ርዕስ የተለያዩ ምሁራንና የህብረተሰብ ተወካዮችን ያሳተፈ የቶክሾዉ ፕሮግራም ተዘጋጀ

    ህዳር 29 ለ17ኛ ጊዜ የሚከበረውን የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓልን አስመልክቶ በድሬዳዋ አስተዳደር መገናኛ ብዙሀን ድርጅት፣ በድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤትና በድሬዳዋ አስተዳደር መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የጋራ አዘጋጅነት “ፌደራሊዝም፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነትና ህገ-መንግስታዊ ” በሚል መሪ ቃል የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውይይት ተደርጓል።

    በቶክ ሾዉ ፕሮግራሙ ላይ በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የህግ ኮሌጅ ዲን የሆኑት አቶ ሮሀ ጴጥሮስ፣ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ከስነ-ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ክፍል አቶ ኬና ከበደ እንዲሁም የህግ ባለሞያ የሆኑት አቶ ሰብስቤ መኮንን ፌደራሊዝም ህብረብ ሔራዊነትና ህገ-መንግስታዊነት ለሀገራዊ አንድነት ያለው ፋይዳ ምንድነው በሚል ሰፋፊ ሀሳቦችን በማንሳትና በመተንተን ከተሳታፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

    የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የፌደራሊዝም ስርዓት ለሀገራችን ምን እንዳበረከተ እንዲሁም ህገ-መንግስታችን ለአንድነታችን ያለውን ፋይዳ በማንሳት ያላቸውን ሀሳብ ተናግረዋል።

    በውይይቱ ላይ ከሀይማኖት አባቶች፣ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከድሬዳዋ ወጣቶች ፌደሬሽን፣ ከሴቶች ፌደሬሽን፣ ከድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት፣ ከሚዲያ ተቋም እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።