በድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኙ ሲቪል ሰርቪስ ተቋማት 17ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ሕብረብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም!” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ኩነቶች ሲከበር የቆየ ሲሆን በዛሬው እለትም የድሬዳዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ከፍተኛ አመራሮች፣ የማኔጅመንት አባላት፣ በአስተዳደሩ የሚገኙ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት የሰው ሀብት ኃላፊዎች እና ከሁሉም የአስዳደሩ የመንግስት ተቋማት የተወጣጡ የመንግስት ሠራተኞች የተሳተፉበት የማጠቃለያ ፕሮግራም በተለያዩ ኩነቶች ተከብሯል።
በማጠቃለያ ፕሮግራሙን በንግግር የከፈቱት የድሬዳዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀይር ሀጂኑር እንደተናገሩት የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተጣለበትን ሕገ-መንግስታዊ ኃላፊነት መሰረት በማድረግ ሚያዝያ 21 ቀን 1998 ዓ.ም ባካሄደው በ3ኛው የፓርላማ ዘመን 1ኛው ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔው የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት የፀደቀበትን ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም በየዓመቱ በተለያዩ መርሀ-ግብሮች እንዲከበር ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ በዓሉ ከሕዳር 29 ቀን 1999 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች አዘጋጅነት በድምቀት ሲከበር መቆየቱን ገልፀው ዘንድሮም በአስተዳደራችን ሲቪል ሰርቪስ ተቋማት 17ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል <<ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም>> በሚል መሪ ቃል በተለያዩ መረሀ ግብሮች ስናከብር ቆይተን ዛሬ ማጠቃለል ችለናል ብለዋል።አቶ ሀይር አክለውም የዘንድሮው በዓል በሲቪል ሰርቪስ ተቋማት በልዩ ሁኔታ ማክበር ያስፈለገበት ዋንኛ አላማም በአስተዳደራችን የመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞች ከተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተውጣጡ በመሆናቸው የዕርስ በዕርስ ትስስራቸውን በይበልጥ በማጠናከር እና በብዝኃነት ላይ የተመሰረተ ሕብረብሔራዊ አንድነታቸውን እንዲያጎለብቱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተለይም ድሬዳዋ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በሰላም፣ በፍቅር፣ በመደጋገፍ እና በመተባበር በጋራ የሚኖሩባት ተንሿ ኢትዮጵያ በመሆኗ ይህንኑ መልካም እሴታችንን ለማስቀጠል ይቻለን ዘንድ በመንግስት ተቋማት የምትሰሩ ሲቪል ሰርቫንቶች በምትሰሩባቸው ተቋማት ውስጥ ይህንኑ የአብሮነት እሴት ይበልጥ በማጎልበት እና በተሰማራችሁበት የሞያ መስክ በተሻለ የአገልጋይነት ስሜት ህብረተሰቡ ከናንተ የሚፈልጋቸውን አገልግሎቶች በሚፈለገው ጊዜ እና ጥራት በመስጠት የጀመርነውን የበለፀገች ኢትዮጵያን የመገንባት ጥረት እውን ለማድረግ የበኩላችሁን ልትወጡ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በማጠቃለያ ፕሮግራሙ <<የሕብረ ብሄራዊ የፌዴራል ስርዓት ምንነት፤ ባህሪያት እና የኢትዩጵያ ነባራዊ ሁኔታ>> በሚል ርዕስ የተወጋጀ ሰነድ በአቶ ዮሴፍ ሞገስ ከቀረበ በኃላ ሰፋ ያለ ውይይት የተደረገ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችም ውይይቱ የመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰቦ አህመድ ምላሽ እና ማብራሪያ ሰተውበታል። በመጨረሻም የተለያዩ የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የባህል ሙዚቃዎች እና ውዝዋዜዎች ቀርበው ፕሮግራሙ ተጠናቋል።


