ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት በራካታ ዓመታት የውጪና የውስጥ እርስ በእርስ ግጭቶችና ጦርነቶችን አሳልፋለች፡፡ በዚህም ምክኒያት በፖለቲካው፣ በማህበራዊውና በኢኮኖሚው ዘርፍ ትልቅ እመረታ ማምጣት ሲገባት በተቃራኒው ከድጡ ወደ ማጡ እያለች እዚህ ደርሳለች፡፡ የሚገርመውና የሚያሳዝነው ግን አብዛኛዎቹ የውጪም ሆነ የውስጥ እርስ በእርስ ግጭቶች የተከሰቱት በተሳሳቱ ወሬዎችና ሀገራችንን የማተራመስ አጀንዳ ያነገቡ ኃይሎች በሚያቀነባብሩት የሚዲያ ወሬ ድግስ ነው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከውስጥም ሆነ ከውጪ ችግሮቿ ተላቃ በሁለት እግሮቿ በመቆም ከተመጽዋችንት ተላቃ መጽዋች እንድትሆን የሁላችንም ሀገር ወዳዶች ፍልጎትና ናፍቆት ነው፡፡ ይሁን እንጅ ይህ እንዳይሆን ሁሌም ሀገራችንን በሥጋት የሚመለከቷት ታረካዊ ጠላቶች አሉ፡፡ እነዚህ ጠላቶቿ መልክና ባህሪያቸውን እየቀያየሩ ብር ፈንድ በማድረግ የውስጥም የውጪም ቅጥረኞችን አሠማርተው እስካሁን ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡ የበሬ ወለደ ወሬዎችን ከመፈብረክ እስከ ማሸበር፤ ልዩነቶችን በተሳሳቱ መረጃዎች ከማራገብ መሣሪያዎችን አቀብሎ ብሄርን ጀብሄር እስከ ማጋጨት ብዙ ርቀት ሄደዋል፡፡
መንግስት በጊዜው ሊፈቱ የሚገባቸውን የህዝብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተለያዩ የውስጥ እና የውጪ ችግሮች ሊፈታ ባለመቻሉ ህዝብን ማስቆጣቱ እውነታ ቢኖረውም ሲያደቡ የነገሩ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ከሩቅ ሆነው የፎከሩትን በቅርብ ለመተግበር ይህን ሁኔታ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅመውበታል፡፡ ሌላው ከአንድነትና ኢትዮጵያዊነት ይልቅ ብሄርን መሠረት ያደረገ እንቅስቃሴ በማወቅም ባለማወቅም ስለነበረ የሀገር ውስጥ ስግብግብ ኪራይ ሰብሳቢዎችና ታሪካዊ ጠላቶቻችን ይህን አጋጣሚ አንደ ጥሩ መደበቂያ ምሽግ ሲጠቀሙበት ነበር፤ እየተጠቀሙበትም ነው፡፡
የሐይማኖትን እና የብሄርን ካባ ለብሰው የሐይማኖት እና የብሄር ተቆርቋሪ በመምሰል ሓይማኖትን ከሐይማኖት ፣ ብሄርን ከብሄር በማጋጨት ሀገራችንን ማባሪያ ወደ ሌለው ትርምስ ውስጥ በማስገባት ግር ግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ የህዝብ ስልጣን ላይ ለመቆናጠጥ ባይሳካላቸውም ብዙ ተፍጨርጭረዋል ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የበሬ ወለደ የፈጠራ ወሬያቸውን ሲመቻቸው ባገኙት የመድረክ አጋጣሚ በቀጥታ በማውራትና የነሱ ልሳኖች በሁኑ አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች መለፈፋቸውን ተያይዘውታል ፡፡ በተለይ በዩትዩብና በፌስ ቡክ ላይ እየተቀነባበሩ ያለገደብ የሚለቀቁ መረጃዎች በምክኒያትና በተጨባጭ መረጃ የማይመሩ ዜጎቻችን ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡
መንግስት የፍቅር፣ የይቅርታና የመደመር ጥሪ በይፋ አቅርቦ ሁሉም ወደ ሀገሩ ገብቶ የራሱን በጎ አስትዋፅዖ እንዲያበረክት ዕድሉ ተመቻችቷል፡፡ ትክክለኛው ዲሞክራሲ እንዲጎለብትና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ ካለው ቁርጠኝነት በመነሳት መስዋዕትነት የሚጠይቅ ቢሆንም መንግስት ይህን መንገድ መከተልን መርጧል፡፡ ነገር ግን እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ዛሬም ልዩነቶችን በማጦዝና በማራገብ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲበራከትና የጀመርነው የለውጥ ጉዞ እንዲጨናገፍ በትጋት እየሠሩ ናቸው፡፡
ለዚህ ደግሞ እንደ ዋና ስትራቴጂ እየተጠቀሙ ያሉትየ በማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚለቀቁ የፈጠራ ወሬዎችን በማሰራጨት ነው፡፡ ጦርነት ከፈታው ወሬ የፈታው ይብሳል ነውና ብሂሉ እጅግ ወድ ዋጋ በጠየቀው ህዝባዊ ትግል እውን የሆነውን ህገ-መንግስትና ህገ-መንግስታዊ ሥራዓት ለመጠበቅ በማህበራዊ ሚዲያዎች ከሚለቀቁ ወሬዎች ራሳችንን በመጠበ ቅ የነዚህን የጥፋት ኃይሎች የማተራመስ ተልዕኮ በጋራ ልናከሽፈው ይገባል ፡፡
የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ
ድሬዳዋ
25/01/2011ዓ.ም


