የድሬዳዋ ኢህአዴግ ሴቶች ሊግ 4ኛ መደበኛ ጉባኤ “አንድነትና ብልፅግና ለሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት” በሚል መሪ ቃል ህዳር 21 እና 22 ተካሂዷል፡፡
ሊጉ 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት ንግግር ያደረጉት የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብደላ አህመድ እንደተናገሩት የኢህአዴግ እንቅስቃሴ ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለአስተዳደሩ ሆነ ለመላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ህዝቦች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት መረጋገጥ የሴቶች ሊግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል፡፡
ምክትል ከንቲባው አክለውም ሴቶች ተሳታፊና ተጠቃሚነት እንዲሁም የህዝቦችን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በተደራጀ የሴቶች ንቅናቄ በመፍታት ሰላም፣ ልማትና ፍትህ እንዲረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የድሬዳዋ ኢህአዴግ ሴቶች ሊግ ሊቀመንበር ወ/ሮ አይናለም ተዘራ ለጉባኤ ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት ከሰላምና ፀጥታ መደፍረስ ጋር ተያይዞ ዋንኛ ተጎጂ ሴቶች በመሆናችን ግጭትን በመከላከል ረገድ ሴቶች ቀዳሚ ድርሻ እንዲኖራቸው በመግለፅ በአሁን ወቅት እንደ ሀገር ሴቶች የአመራርነት የውሳኔ ሰጪ አካል እንዲሆኑ እየተደረገ እንደመሆኑ በድሬዳዋ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል ብለዋል፡፡
ሊጉ በ4ኛ መደበኛ ጉባኤው ባለፉት ሁለት አመታት ተኩል የተከናወኑ ተግባራት የተገመገመ ሲሆን ከፌደራልና የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ሴቶች ሊግ ጨምሮ የሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶች በጉባኤው መክፈቻ ተገኝተው የድጋፍና የአጋርነት ንግግር አድርገዋል፡፡
የድሬዳዋ ኢህአዴግ ሴቶች ሊግ አዲስ ሊቀመንበር ምርጫ አካሂዷል፡፡ የሊጉ ሊቀመንበር ወ/ሮ ኢንቲሳር አብዱረህማን ምክትል ሊቀመንበር ወ/ሮ ሰላማዊት አስፋው የተመረጡ ሲሆን 9 የስራ አስፈጻሚ አባላትም ተመርጠዋል፡፡
በ4ኛ መደበኛ ጉባኤው የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አብደላ አህመድ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አብዱሰላም መሐመድ፣ የካቢኔ አባላት ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡


