ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ወደ 40 ቢሊዮን ብር ገደማ እንደሚያስፈልግ የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት አስታወቀ።
ለግድቡ ግንባታ በአጠቃላይ 160 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ እና እስካሁን ድረስም 121 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን በጽ/ቤቱ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ለኢዜአ ተናግረዋል።
በ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለግድቡ 507 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡንም ገልጸዋል።
በዚህም በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም ብቻ 109.9 ሚሊዮን ብር፣ በነሐሴ ወር ከ152 ሚሊዮን በላይ እንዲሁም በመስከረም ወር 197 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
በመስከረም 2013 ዓ.ም የተገኘው 197 ሚሊዮን ብር ገቢ እስከዛሬ ለግድቡ ግንባታ በወር ከተሰበሰበው ገቢ ከፍተኛው መሆኑን ተናግረዋል።
ሕዝቡ እስካሁን ያሳየውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል እና የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ድጋፉን እንዳያቋርጥ ጥሪ አቅርበዋል።
የግድቡ የግንባታ ሂደት 76 በመቶ መድረሱን ወቅታዊ መረጃዎች ያሳያሉ።
ምንጭ EBC


