ከሁሉ በማስቀደም የሀገራችን ህዝቦች ሉአላዊ የስልጣን ምንጭ መሆናችንን ያረጋገጠው ህገ-መንግስት፤ የዲሞክራሲያዊ ስርአታችን መሰረት መሆኑን በመረዳት፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ቃል ኪዳናቸውን በጋራ ለሚያድሱበትና በታላቅ ድምቀት ለሚያከብሩት ለዚህ ታላቅ ህዝባዊና ሀገራዊ በአል እንኳን አደረሰን አደረሳችሁ በማለት፤ ሁላችሁንም እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡
የህገ መንግስታችን መሰረታዊና ዋነኛ አላማዎች፤ የዲሞክራሲ እሴቶች ማክበር፤ ማህበራዊ ፍትህንና የዜጎችን መብት ማረጋገጥና፤ የዜጎችን ህይወት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲሻሻል ማስቻል በመሆኑ፤ ከዚህ መሰረታዊ አላማ አንጻር የህገ-መንግስቱን ስኬቶቸና ተግዳሮቶች ለመቃኘት የሚያስችለውና፤ በየአመቱ የብሔር ብሔረሰቦችን በአል ስናከብር የምናካሂደው ሀገራዊ ሲምፖዚየም ከፍተኛ ትርጉም የሚሰጠው ነው፡፡
ይህ በመሰኩ ምሁራንና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ የምናካሄደው ሲምፖዚየም፤ በአንድ በኩል በህገ-መንግስቱና በፌደራል ስርአቱ የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠልና በተለይም የህገ-መንግስቱን እሴቶች በተገቢው መልኩ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ፤ ሊከናወኑ ከሚገባቸው ጉዳዮች እንደ አንዱ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ሲሆን፤ በሌላ በኩል አሁን ሀገራችን የገጠሟትን ተግዳሮቶች በዘላቂነት ለመሻገር የሚቻለው፤ በህዝቦች ፍላጎት የተመሰረተውን ህጋዊና ዲሞክራሲያዊ ስርአት በማክር በመጠበቅና አጠናክሮ በማስቀጠል መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
አሁን የምንገኝበት ምዕራፍ፤ እንደ ሀገር በአንድ በኩል ሀገራችን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ወደ ለውጥ ምዕራፍ የገባችበትና፤ በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ ያሉበት ሲሆን፤ በሌላ በኩል ለሀገርና ለወገን ቅድሚያ በመስጠትና ውጤታማ በመሆን ሀገርንና ትውልድን ለማሻገር የሞት ሽረት ትግል ላይ የምንገኝበት ወቅት በመሆኑ፤ ይህን ታላቅ ህዝባዊና ሀገራዊ ራዕይ በመረዳት፤ በመሰዋእትነት እያሻገሩን ላሉ ጀግኖቻችን ክብርና ምስጋና የምንሰጥበት በመሆኑ፤ በዚህ አጋጣሚ የጦር ግንባሩን ጨምሮ በሁሉም መስኮች ለሀገራችው በመዋደቅ ላይ ላሉ ጀግኖቻችን የከበረ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡
የፌደራል ስርአታችን ተጨባጭ ለውጥ ካመጣባቸውና፤ በተለይም በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየታዩባቸው ካሉ አካባቢዎች፤ የምስራቋ የኢንዱስትሪ በር ድሬዳዋ አንዷ ስትሆን፤ በአስተዳደራችን በአሁኑ ወቅት የኢንዱስትሪ ልማት 41 በመቶ፤ የአገልግሎት ዘርፍ 53 በመቶ ድርሻ በመያዙ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፍ ከአስተዳደራችን አጠቃላይ ኢኮኖሚ 94 በመቶ ድርሻ ይዟል፤ ይህም ድሬዳዋ በ2022 የምስራቅ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፈርጥ ለመሆን የያዘችውን ራዕይ ለማሳካት በትክለኛው መንገድ ላይ መሆኗን የሚያሳይ ነው፡፡
የኢንዱስትሪ ልማት መረጋገጥ የንግድና የአገልግሎት ማዕከልነትን ለማሳካት ካላው ወሳኝ ድርሻ አንጻር አስተዳደራችን ለዚሁ መስክ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ የሚገኝ ሲሆን አምራች ኢንዱስትሪ ሰፊ የስራ እድልን የሚፈጥር፤ የገቢ አቅሙን የሚያሻሻል፤ መዋቅራዊ ለውጥን ለማረጋጋት የሚረዳና ለእድገታችን ዛላቂነት ወሳኝ በመሆኑ የኢንዱስትሪ ልማት በማረጋገጥ አጠቃላይ ኢኮኖሚያችንን በፈጣን ሁኔታ ማሳደግ በቀጣይ አስር አመታትም በአስተዳደራችን በያዝነው እቅድ ትኩረት የሰጠነው ጉዳይ ነው፡፡
ባለፉት አመታት በተለይም ከለውጡ ወዲህ ስኬታማ ስራ ከሰራንባቸው መስኮች የአስተዳደራችንን ሰላም ማስጠበቅና ድሬዳዋን እንደ ወትሮ ሁሉ በሰላሟና በፍቅሯ የምትታወቅ ከተማ ማድረግ አንዱ ሲሆን፤ በዚህ ረገድ የተገኘው ውጤት አበረታች ነው፡፡
በአጠቃላይ በቀጣይም በማክሮ ኢኮኖሚ በኢኮኖሚያዊ ልማት፤ በማህበራዊ ልማትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ለውጥን ለማምጣት ጠንክረን እንደምንሰራ በዚሁ አጋጣሚ እየገለፅኩ፤ የሁላችሁም ከተማ በሆነችው ድሬዳዋ የሚኖራችሁ ቆይታ የተሳካ እንዲሆን እመኛለሁ።
“የላቀ ክብር ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ሲሉ በመዋደቅ ላይ ላሉ ጀግኖቻችን”


