በድሬዳዋ አስተዳደር በሌማት ቱሩፋትና በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ላይ እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች አበረታች መሆናቸው ተገለፀ::

የኢፌድሪ ማዕድን ሚኒስተር ክቡር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ከድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀርና ከመስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በጋራ በመሆን በዛሬው ዕለት በድሬዳዋ አስተዳደር በሌማት ቱሩፋት፣ በከተማ ግብርናና በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸውም የዶሮ እርባታ፣ የወትተና የወተት ውጤት ስራዎችን፣ የከብት እርባታን፣ የአትክልትና የፍራፍሬ እርሻዎችን፣ የከተማ ግብርናን፣ የውሃ ግድቦችን፣ በሀርላ የሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎችን በአጠቃላይም የሌማት ቱሩፋት ስራዎችን ተመልክተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ያነጋገርናቸው ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ የዚህ ጉብኝት ዋነኛ አላማ በድሬዳዋ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ምን ይመስላሉ የሚለውን ለመመልከትና መልካም ጅምሮችን ለማበረታታትና ለማጠናከር፤ እንዲሁም ልምዶችን ለመቅሰም መሆኑን ገልፀዋል።

ኢንጂነር ሀብታሙ አያይዘውም በዛሬው የጉብኝት መርሀ-ግብር በድሬዳዋ እየተሰሩ የሚገኙ አጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴዎችን መመልከታቸውን ገልፀው፤ ወጣቶች በመደራጀትና ውሃ በማውጣት አትክልትና ፍራፍሬን በማልማት ላይ እንደሚገኙ መመልከታቸውንና ይህም ለሀገራችን ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በሌማት ቱሩፋቱም በርካታ አበረታች ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የጠቆሙት ኢንጂነር ሀብታሙ፤ በተለይም ከጥቂት አመታት በፊት ደረቅ የነበሩ ቦታዎች አሁን ላይ ምንም አይነት መሬት ፆሙን ማደር የለበትም በሚል ወጣቶች በመረባረብና ወደ ስራ በመግባት ማልማታቸውንና ይሄም የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

በመጨረሻም ኢንጂነር ሀብታሙ በድሬዳዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች አበረታችና ለሌሎችም አካባቢዎች በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም ይህንን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በኤደን ሳሙኤል

ፎቶ:- ቴድሮስ ልዑልሰገድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *