በስነ ምግብ የዳበረ አኗኗርን ለመመስረት የሚዲያ ባለሞያዎች እገዛ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ

    በድሬዳዋ የሚገኙ ሴክተር ተቋማት የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎችም ሆነ የሚዲያ አካላት የተመጣጠነ ምግብ ለእናቶችና ህፃናት ያለውን ፋይዳ በአግባቡ አውቀው ግንዛቤ የመፍጠር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ፡፡

     

    የድሬደዋ አስተዳደር ጤና  ቢሮ ከድሬዳዋ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ጋር በመቀናጀት ለኮሙዩኒኬሽን ባለሞያዎችና ለጋዜጠኞች  የተመጣጠነ ምግብ ለእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ ያለውን ጠቀሜታ የሚያሳይ ስልጠና ሰጥቷል ፡፡

    በሀገራችን ያሉ እናቶችና ህጻናት ከቅድመ ወሊድ እስከ ድህረ ወሊድ ባሉ ጊዜያት ብሎም ህጻናቱ ሁለት አመት እስኪሞላቸው ከተመጣጠነ ምግብና ቪታሚን ኤ እጥረት ጋር ተያይዞ ለሚከሰተው የህጻናት መቀንጨር በሽታ እንዳይዳረጉ የተመጣጠኑ ምግቦችን በአግባቡና በወቅቱ ሊወስዱ ይገባል፡፡

    አቶ ሚካኤል እንዳለ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የመረጃ አካላትን የማፍራትና የማብቃት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመድረኩ እንደተናገሩት በአብዛኛው የአስተዳደራችን  እናቶች ከግንዛቤ እጥረት ጋር ተያይዞ ባላቸው አቅም ጤናማ የስነ ምግብ አመጋገብ ሲያዘወትሩ አይስተዋልም ፤ ስለሆነም  ይህን የግንዛቤ ክፍተት በመሙላት ረገድ የሚዲያ አካላት በቂ ግንዛቤን ጨብጠው በተለያዩ መንገዶች ግንዛቤን እንዲፈጥሩ በማለም ይህን መሰል ሙያዊ ስልጠና  ለሚዲያ ባለሞያዎች ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

    ስልጠና ብቻውን ግብ አይሆንም ያሉት አቶ ሚካኤል ከስልጠና መልስ ባለሙያው ግንዛቤውን ወደ ማህበረሰብ በተለያዩ የሚዲያ መንገዶች እንዲያወርድም ጠይቀዋል፡፡

    በድሬዳዋ ጤና ቢሮ የእናቶችና ህጻናት የስርዓተ ምግብ ኤክስፐርት ሲ/ር ደመቁ መኮንን በበኩላቸው አሁን ላይ በአስተዳደሩ የከተማና ገጠር ጤና ተቋማት ላይ የእናቶችና ጨቅላ ህፃናት የስርዓተ ምግብ ጤና ላይ የጤና ባለሙያውን በማብቃት ማህበረሰቡ በጤና ተቋማቱ አስፈላጊውን ግንዛቤም ሆነ ቪታሚኖች በበቂ ሁኔታ እንዲያገኝ እየተሰራ ቢሆንም አሁንም ግን ግንዛቤው ወደ ማህበረሰቡ እንዲወርድ የሚዲያ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

     እናቶች ከእርግዝና ወቅት ጀምሮ በጤና ተቋማት ላይ ለ1ሺ ቀናት ማለትም ልጃቸው ሁለት አመት እስኪሞላው በቂ ክትትልን በማድረግ ብሎም የተመጣጠነ ምግብን በመመገብ ልጆቻቸውን ከመቀንጨርና ተያያዥ ከሆኑ ህመሞች ሊታደጉ ይገባል ያሉት ሲስተር ደመቁ በዚህም ሰልጣኞች የድርሻቸውን ሊያበረክቱ እንደሚገባ ጥሪ አስተላልፈዋል ፡፡