አቅም ለመገንባት የሚሰጡ ስልጠናዎችን ወደ ተግባር በመለወጥ የሚዲያ እና የኮሙዩኒኬሽን ሙያን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ::

    ለኦዲዮ ቪዥዋል ባለሞያዎች ለ10 ቀናት የዘለቀ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
    የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ /ኦ.ቢ.ኤን/ ጋር በመተባበር ለ10 ቀናት የዘለቀ የኦዲዮ ቪዥዋል ስልጠና ሰጥቷል፡፡
    ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ በመጡ ሁለት ባለሞያዎች በተሰጠው ስልጠና ከሴክተር ተቋማትና ከቀበሌዎች የተውጣጡ የኦዲዮ ቪዥዋል ባለሞያዎች፣ የህዝብ ግንኙነት ባለሞያዎችና ሀላፊዎች በስልጠናው ተካፋይ ሆነዋል፡፡ ስልጠናው የካሜራ እና የኤዲቲንግ ጽንሰ ሃሳቦችን ከማስጨበጥ ባሻገር በአብዛኛው ተግባር ተኮር መሆኑ ሰልጣኖች ለቀጣይ ስራቸው ትልቅ ስንቅ እንደሚሆናቸው በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ ተገልጿል፡፡
    ለ10 ቀናት የቆየው ስልጠና ማጠናቀቂያ ላይ ሰልጣኞች በቡድን በቡድን ሆነው በስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ የሰሯቸውን ፕሮግራሞች አቅርበው ከአሰልጣኞቹ ገንቢ አስተያየቶችን ተቀብለዋል፡፡
    ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ የመጡት ባለሙያዎች ሠልጣኞች ስልጠናውን በጥብቅ ሥነ-ምግባር መከታተላቸውን በመግለፅ ለሰልጣኞቹ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
    ከስልጠናው ብቻ የሚገኝ የዕውቀት ግብዓት በቂ ባለመሆኑ ሠልጣኞች ከስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት በደንብ ወደ ተግባር እንዲለውጡ አስፈላጊ የኦዲዮቪዥዋል ቁሳቁሶችን ማሟላት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በቀጣይም ስልጠናዎችን ለመስጠት በጎ ፈቃዳቸውንም አሰልጣኞቹ አሳይተዋል፡፡
    የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቅያስ ታፈሰ በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ ባስተላለፉት የመዝጊያና የሥራ መመሪያ ንግግራቸው ሠልጣኞች አቅም ለመገንባት የሚሰጡ ስልጠናዎችን ወደ ተግባር በመለወጥ የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን ሙያን ማሳደግ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
    አቶ እስቅያስ ሰልጣኞች በጥብቅ ሥነ-ምግባር ስልጠናውን በመከታተላቸው ምስጋናን ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይ በተለያዩ የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን ዘርፎች ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚሰጡ ገልፀዋል፡፡
    የኦዲዮቪዥዋል መገልገያ ቁሳቁሶችን ለማሟላት ቢሮው በቀጣይ እንደሚሰራ በመግለፅ የግብዓቶች አለመሟላትን ምክንያት ባለማድረግ ባሉት ቁሳቁሶች ስራዎችን በተሻለ መንገድ ለመስራት ጥረት ማድረግ ግን ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
    በስልጠናው ማብቂያ ላይ ከሰልጣኞች ለአሰልጣኞች ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡