ከ 38 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የድሬዳዋ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ህንፃ ተመረቀ፡፡

    በድሬዳዋ አስተዳደር ልዩ ስሙ ከዚራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተገነባው የመጀመሪያ ደረጃና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ህንፃ የተመረቀ ሲሆን በምረቃው ስነ-ስርዓቱ ላይም ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡
    በአስተዳደሩ የተገነባው የመጀመሪያ ደረጃና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ህንፃ የፍትህ ስርዓቱን ለማጎልበት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውና ህንፃውም የተቋሙን አገልግሎት ምቹ ለማድረግ ይቻል ዘንድ እጅግ ዘመናዊ በሆነ መልኩ መሰራቱን የድሬዳዋ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሀመድ ተናግረው ለህንፃው ግንባታም ከ 38 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንና ለግንባውም መሳካት አስተዋፆ ላደረጉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቶ አብዲ በእለቱ አቅርበዋል፡፡
    በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ በበኩላቸው በአስተዳደሩ በፕሮጀክቶች መጓተት ብዛት ጉዳት በሚስተዋልበት በዚህ ወቅት ተገንብቶ ለምርቃት የበቃው የፍርድ ቤቱ ህንፃ የሚያበረታታና አርአያ እንደሚሆን ተናግረው በቀጣይም ፍርድ ቤቱ ከፌደራል ፍርድ ቤት ጋር በጋራ በመሆን መስራት እንደሚገባም ነው ወሮ ፈጡም ሙስጠፋ የተናገሩት፡፡
    በምረቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ ለተገኙ ተሳታፊ ለሆኑ እንግዶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለ-ህንፃው አጠቃላይ ሁኔታ ገለፃ ያደረጉት የፕሮጀክቱ ተቋራጭ ኢንጂነር መላኩ ተስፋዬ ህንፃው ዘመናዊ ግብዓቶችን ማሟላቱንና የህንፃውን ግንባታም በተያዘለትና ጊዜና በጥራት ለመስራት በትኩረት እንደተሰራና ይህም ተግባር በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይም እንደሚቀጥልም ኢንጂነር መላኩ ተናግረዋል፡፡