ዜና ታሪካዊው የድሬዳዋ ምድር ባቡር የመንገደኖች ተርሚናል በ 13.5 ሚሊየን ብር ጥገና ሊደረግለት እንደሆነ ተገለፀ

የድሬደዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ፅ/ቤት ከኢትዮጲያ ቅርስ ባለስልጣን መ/ቤት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ታሪካዊውን የድሬዳዋ ምድር ባቡር የመንገደኖች ተርሚናልን ለመጠገን በዛሬው ዕለት የውል ስምምነት የፊርማ ስነ-ስርዓት አከናወነ፡፡

በፊርማ ስነ-ስርአቱ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬደዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ መካኤል እንዳለ የድሬደዋ ምድር ባቡር ረጅም እድሜ ያስቆጠረ በመሆኑና የድሬደዋን ታሪክ የያዘ በመሆኑ ለከተማችን ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለሁ አንስተው፤ ይህንን ታሪካዊ ቅርስ ከነሙሉ ገፅታው ለትውልድ ማሸጋገር አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በዚህም ከኢትዮጲያ ቅርስ ባለስልጣን መ/ቤት ጋር በመተባበር ጥናቶች እንደተደረገና ጥገና ለማድረግ በዛሬው ዕለት ውል እየተፈራረሙ መሆኑን ተናግረዋል ለዚህም ባለስልጣኑን አመስግነዋል፡፡

የኢትዮጲያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ህይወት ሀይሉ በበኩላቸው የድሬደዋ ምድር ባቡር ተርሚናል በትራንስፖርት ቱሪዝም ውስጥ በርካታ ታሪክ ያለው ግንባር ቀደም ተቋም መሆኑን ገልፀው፤ ይህንን ታሪክ ጠብቆ ለማቆየት ጥገና ማድረግ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጲያ ቅርስ ባለስልጣን ቅርፆችን፣ የመጠበቅ የመንከባከብና የመጠገን ሀላፊነት ያለበት በመሆኑ የድሬዳዋ ምድር ባቡር የመንገደኖች ተርሚናል ላይ የረጅም ጊዜ ጥናት በማከናወን ያሉትን ችግሮች በመለየት እድሳት የሚያስፈልግበትን ቦታ በመለየት ለመጠገን መፈራረማቸውንና በዚህም ስራው በ9 ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅና 13.5 ሚሊየን ብር እንደሚፈጅም ወ/ሮ ህይወት ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ስራውም በጥራትና የቅርስ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ እንደሚሰራ ያነሱት ዳይሬክተሯ ከተለያዩ የአለም ሀገራት የተውጣጡ የድሬዳዋ አስተዳደር ልጆች ፣ ወዳጆች እንዲሁም ከፈረንሳይ ፣ ከጅቡቲ፣ ከኒጀር፣ ከማሊና ከዩኤስኤን ጨምሮ ከሌሎች የዓለም ሀገራትም የመጡ የዲያሎግ ሂዩማኒቲ አባላት እና ተሳታፊዎች በዚህ በፊርማው ስነስርአት ላይ በመገኘታቸው መደሰታቸውን ገልፀው ተቋሙ ላይ የራሳችሁን አሻራ አሳርፉ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ከፊርማው ስንስርዓት በመቀጠልም ከተለያዩ የአለም ሀገራት የተውጣጡ የድሬዳዋ አስተዳደር ልጆች ፣ ወዳጆች እንዲሁም ከፈረንሳይ ፣ ከጅቡቲ፣ ከኒጀር፣ ከማሊና ከዩኤስኤን ጨምሮ ከሌሎች የዓለም ሀገራትም የመጡ የዲያሎግ ሂዩማኒቲ አባላት እና ተሳታፊዎች የባቡር ሽርሽር አከናውነዋል በዚህም ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *