የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ወደ ስራ መግባቱ ጥቅሙ ለድሬደዋ መስተዳደር ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች ክልሎችም መሆኑ ተገለፀ።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል በዛሬው ዕለት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሃር ንግግር ያረጉ ሲሆን ዛሬ ይህ መማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ተመርቆ ወደ ስራ መግባቱ የማህበረሰቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ የመለሰ መሆኑን አንስተው፤ ሆስፒታሉ የዩኒቨርስቲው አንዱ ማሰልጠኛ ሆኖ ጎን ለጎንም ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት አጠናክሮ እንዲቀጥል በቀጣይ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶች መሟላት እንደሚገባቸውና አካባቢውንም ምቹና ሳቢ ማድረግ እንደሚገባ አቶ ከድር ጠቁመዋል።

ሆስፒታሉ ወደ ስራ መግባቱ ጥቅሙ ለመስተዳደሩ ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች ክልሎች ማለትም ለሶማሌ ክልል፣ ለኦሮሚያ ክልል እንዲሁም ከጅቡቲና ባጠቃላይም ለአጎራባች ክልሎች አገልግሎት በመስጠት እንደሚጠቅም ክቡር ከንቲባው ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴዔታ የሆኑት ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው ሆስፒታሉ በከፊል ወደ አገልግሎት መግባቱ በምሥራቁ የሀገሪቱ ክፍል የተሻለ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል። ድሬዳዋ የምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል እንመሆኗ፤ በከተማዋ እያደገ ያለውን የጤና አገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት የሆስፒታሉ ጠቀሜታ የጎላ ነው በማለትም ተናግረዋል። በቀጣይ ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ ወደ አገልግሎት እንዲገባ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርግ ሚኒስተር ዴኤታው ገልፀዋል።

ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ይህ ሆስፒታል 400 የሕሙማን አልጋዎች፣ 4 ዋና እና 4 መለስተኛ የቀዶ ጥገና ክፍሎች፣ የማዋለጃ ክፍል፣ የፅኑ ሕሙማን ክፍል፣ ፋርማሲዎች፣ የጥናት ማዕከላት በውስጡ ይዟል።

በምርቃት ስነስርአቱ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሀር፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፈቲያ አደን፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ከሪማ አሊ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ ቤት ሀላፊ የተከበሩ ኢብራሂም ዩሱፍ፣ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባ አደም፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ጽጌሬዳ ክፍሌ፣ የኢፌድሪ የጤና ሚኒስተር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ድጉማ እንዲሁም የመስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *