በአስተዳደራችን የበጋ ወራት የበጎፈቃድ መርሃ ግብር የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶች የመልሶ ግንባታ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ የበጋ ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራ ላይ ህብረተሰቡን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በድሬደዋ አስተዳደር በበጋ ወራት የበጎ ፍቃድ የልማት ተግባራት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች መከናወናቸውን የወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ካሊድ መሐመድ ተናግረዋል፡፡ በዛሬው እለት የተለያዩ ተቋማት በማስተባበር ከ3.5 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነቡ ቤቶች ለችግረኞች ቤተሰቦች ተሰጥተዋል።
በዘንድሮ የበጋ ወራት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ እና የማህበራዊ አገልግሎት ችግሮችን ያቃለሉ የልማት ስራዎች ተሰርተዋል። በእለቱም በተቋማት የተቀናጀ ጥረት ተሰርተው የተላለፉት ቤቶች የበጎ ፍቃድ ልማቱ መሳያ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በበጋ ወራት በየደረጃው የሚገኙ ተቋማትና በጎ ፍቃደኞችን በማስተባበር፣ የትምህርት፣ የደም ልገሳ፣ የተፋሰስ ልማት፣ ማዕድ የማጋራት፣ የአካባቢ ልማትና ፅዳት፣ የስፖርት፣ የችግረኞች አረጋዊያን ቤቶች ግንባታና እድሳት ተጠቃሽ መሆናቸውን ነው አቶ ካሊድ የገለፁት።
ቤቶቹን አስገንብተው ለአራት ቤተሰቦች ያስረከቡት በድሬዳዋ የሚገኘው የኢትዮጵያ የባህርና ሎጀስቲክስ ቅርንጫፍ፣ የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያና የቀበሌ መስተዳድሮች ናቸው።
በቤቶቹ ርክክብ ላይ የተሳተፉት የወረዳ አራት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብዱጀባር ሁሴን እንዳሉት ብዙ ጊዜ የበጎ ፈቃድ ስራ በክረምት ነበር የተለመደው አሁን ላይ በክረምት በቂ ስላልሆነ የሰዎችን ችግር በጊዜ ከመቅረፍ አንፃር በበጋም ጭምር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ ተግባር የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህላችንን የሚያጎለብት የችግረኞችን እንባ የሚያብስ እንዲሁም ያለው የሌለውን እንዲያግዝና እንዲደግፍ ያደርጋል ያሉት ደግሞ የወረዳ አንድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳላህ መሃመድ ናቸው፡፡
የገንደቆሬ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ኢ/ር ዘመድኩን አካሉ በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙ ሲሆን ፖሊስ ፀጥታውን ከማስከበር ባሻገር ለተቸገሩ ወገኖች በሰብዓዊነት ለማገልገል ሁሌም ቀዳሚ ነው ብለዋል፡፡
በአካባቢው ኮሚኒቲ ውስጥ ያሉ ማህበረሰቦችን በማስተባበር፣ ሀብት በማሰባሰብ አቅመ ደካሞችን በመለየት ለተቸገሩ ወገኖች የነበራቸውን ቤት በአዲስ አፍርሶ በመገንባት ዛሬ ለማስረከብ መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ገንደቆሬ ፖሊስ ጣቢያ እና የወረዳ የአራት ፅ/ቤት ብዙ ስራዋች ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ በመሆን መስራታቸውን ኢ/ር ዘመድኩን ተናግረዋል፡፡
ቤት የተላለፈላቸው አቅመ ደካሞች እንደተናገሩት ቤታቸው በክረምት ዝናብ በበጋ ፀሀይ እያስገባ መቸገራቸውን ጠቅሰው አሁን ላይ ይህን ላሰቡ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በበጋ ወራት የበጎ ፍቃድ ስራ የተገነቡ ቤቶች ለአቅመ ደካሞች ከመተላለፉ ባሻገር የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብርም ተካሂዷል፡፡


