የድሬዳዋ አመራሮች በብልጽግና ፓርቲ መርሃ ግብርና ህገ-ደንብ ዙሪያ ተወያዩ

    የብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ያገኟቸውን ውጤቶች ለመንጠቅ ሣይሆን ያጡትን ሁሉ ለመመለስ መመስረቱን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ማዕከላት አስተባባሪ ዶክተር አለሙ ስሜ ተናገሩ።

     

         ዶክተር አለሙ ስሜ ይህን የተናገሩት የድሬዳዋ አመራሮች በብልጽግና ፓርቲ መርሃ ግብርና ህገ-ደንብ ዙሪያ ሲወያዩ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

         በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ወደ ውህድ ፓርቲ ለመሸጋገር የተጀመረው ከ16 ዓመታት በፊት በመሆኑ ዘገየ እንጂ አልፈጠነም፤ በአለም ለረዥም ዓመታት የኖረ ግንባር ኢህአዴግ ብቻ ነው።

         በየቀኑ ከሚለወጥ አለም ጋር ለመስተካከል ከፊል ኢትዮጵያዊያንን ያገለለውን ፀረ-ዴሞክራሲ አሠራርን ቀይሮ ፍትሃዊ ተሣትፎን ለማረጋገጥ ውህደቱ በወሳኝ ጊዜ መጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡

         ክልሎች ራስ በራሳቸው ሲያስተዳድሩ ነበር የሚባለው ሐሰትና በግለሰብ ትዕዛዝ ውሳኔያቸውን የሚለውጡበት አጋጣሚዎች ጭምር መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡

    አራቱም የግንባሩ አባል ድርጅቶች ቢሆኑም እኩል መብት እንዳልነበራቸውም አስታውሰዋል።

         “ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ያገኙትን ለመንጠቅና ለመቀነስ ሣይሆን በጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ ወደ ብልጽግና ለመሻገርና ያጡትን መብቶች ለመመለስ ነው “ብለዋል፡፡

         ክፋፋዩን አደረጃጀት መናድ በራሱ ትልቅ ለውጥ እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር አለሙ ውህደቱን የፈጠሩት ድርጅቶች የፌደራዝም ስርዓት ለመገንባት፤ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ የብሔር ብሔረሰቦችን መብቶች ተቀብለው ለዓመታት ሲታገሉ የነበሩ በመሆናቸው ከአሃዳዊ መንግስት ሥርዓት ጋር የሚያገናኛቸው አንዳችም ነገር እንደሌለ አብራርተዋል።

         ለውጡን ለመቀልበስ በሀገርና በውጭ ሀገር ጭምር ሌት ተቀን እየተሰራ በመሆኑ በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ነዋሪዎች ወደ ብልጽግና የሚደረገው ጉዞ እንዳይሳናከል መረባረብ እንደሚገባም አሳስበዋል።

         “በብልጽግና ፓርቲ ህገ-ደንብ መርሃ ግብር ላይ ጥልቅና ዝርዝር ስልጠና ለአመራሩና በየደረጃው ለሚገኙ አባላትና ነዋሪዎች ይሰጣል” ብለዋል፡፡

         የድሬዳዋ አስተዳደር ካቢኔ አባል አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው “የኢትዮጵያን ህዝብ በሙሉ ያላቀፈው ግንባር ተንዶ የብልጽግና ፓርቲ መመሰስረቱ በራሱ ትልቅ ለውጥና ለዜጎች ተስፋ የሚሰጥ ይሆናል “ብለዋል፡፡

         ታዳጊ ክልሎች አጋሮች በሚል ከፌደራል መዋቅርም ሆነ በሀገር መሠረታዊ ጉዳይ በማግለል የህዝቡን ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብትና ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዳይኖረውና ተጠቃሚ እንዳይሆን መደረጉን ተናግረዋል፡፡

         “ አሁን ወደ ትክክለኛ ፌደራሊዝም ለመምጣት ጉዞ ጀምረናል፤ ተደስተናል”ብለዋል፡፡

         ማህበረሰቡን ስለብልጽግና ፓርቲና ስለለውጡ በአግባቡ ማስገንዘብና የተጀመረውን ለውጥ ዳር ለማድረስ አጋዥነቱን እንዲጠናከር መስራት እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ ሌላው አመራር አቶ መሐመድ ሱሌይማን ናቸው፡፡