የኢህአዴግ ውህደት ወቅቱን የጠበቀ መሆኑ ተገለፀ

    የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/  የውህደቱ ጥያቄ ለረዥም ጊዜ የቆየ በመሆኑ ውህደቱ አሁን ላይ መደረጉ ወቅቱን የጠበቀ መሆኑን  በውህደቱ ዙሪያ ከድርጅት አባላት ጋር ውይይት በተደረገበት ወቅት ተገልጧል፡፡

     

         በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው ገለፃ ያደረጉት በኦ.ዲ.ፒ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የከንቲባው የተፋሰስ ልማት አማካሪ አቶ አብዱጀዋድ መሀመድ የኢህአዲግ የውህደት ጥያቄ ረዥም ጊዜ የቆየ መሆኑን ገልፀው በተለይም በአጋር ድርጅቶች በ10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ተጠይቆ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በሀዋሳው ጉባኤ ጥናት ይደረግበት ተብሎ እንደተወሰነ በማከል፡፡ በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ የኢህአዴግ ምክር ቤት ጥናቱን ለፍፃሜ እንዲያደርስ በተሰጠው ሃላፊነት ጥናቱ እንዲካሄድ ካደረገ በኋላ ጥናቱን መሰረት በማድረግ ውህደቱ እንደተፈፀመ ተናግረዋል፡፡

         የህዝቡ ግፊት ለኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ሁነኛ ምክንያት መሆኑ፣ ባለፉት 4 እና 5 ዓመታት የህዝቡ ቅሬታና ቁጣ እየተባባሰ መምጣቱ ለውህደቱ ምክንያት ናቸው ከተባሉት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ውህደቱ ባይፈፀም የድርጅቱን ህልውና ማስቀጠል አይቻልም ነበር ያሉት አቶ አብዱጀዋድ ይህ ደግሞ በጊዜ ሂደት ድርጅቱን ለመፍረስ ከመዳረግ ባለፈ አግላይነትንም ያስቀጥል እንደነበር ተናግረዋል፡፡

         ውህደቱ ከጨፍላቂነት ይልቅ አካታች ነው የሚሆነው ያሉት አቶ አብዱጀዋድ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ብሄር ብሄረሰቦች ተገቢው ውክልና እንዲኖራቸው በውህድ ፓርቲው ህገ-ደንብ በግልፅ ተቀምጧል ብለዋል፡፡ በሀገራችን ውህድ የፈፀሙ ፓርቲዎች በመዋሃዳቸው ምክንያት በየትኛውም መንገድ እራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸውን ውህደቱ የጣሰ አይደለም ሲሉ ገልፀዋል፡፡

         የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ እስቅያስ ታፈሠ በበኩላቸው የብልፅግና ፓርቲ ዓላማ የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ህብረ-ሃገራዊነቱ የተጠበቀ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባት ዓላማም ያነገበ እንደሆነ አክለዋል፡፡

         ለቀጣዩ ትውልድ ሰላምን ለማውረስ ፓርቲው የትኛውንም የዕርቅ መንገድ ይጠቀማል ያሉት አቶ እስቅያስ ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ልማትና ፍትሃዊነትን ማረጋገጥ፣ ሀብት ፈጠራን የሚያሳድግ ዕውቀት መር ኢኮኖሚን መገንባትና ከተሜና የከተማ ልማትን ማስፋት ከፓርቲው የኢኮኖሚ ፕሮግራሞች ውስጥ ዋናዋናዎቹ እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡ ፍትሃዊነት፣ ጥራት፣ አካታችነትና አግባብነት ያለው የትምህርት ስርዓት እንዲኖር መስራት፣ የኪነጥበብ ማዕከላት ጎልተው እንዲወጡ መታገል በአቶ እስቅያስ ከተጠቀሱ የፓርቲው ማህበራዊ ፕሮግራም ግቦች ውስጥ ይገኙበታል፡፡

         ሀገራዊ ክብርን ማዕከል ያደረገ የውጭ ግንኙነት፣ የብዙዮሽ ዲፕሎማሲን በመጠቀም አለምአቀፍ ተሰሚነታችንን ማሳደግ፣ የኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያንን ተሳትፎ ማሳደግ፣ የመከላከያ ሰራዊታችን የዘመኑን አውደ-ውጊያ የዋጀና ሁሉንም በዕኩል አይን የሚያይ እንዲሆን ማድረግ ከፓርቲው የውጭ ግንኙነት ዓላማዎች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

         የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ውህደቱ ለበርካታ ዓመታት ሲጠየቅ እንደነበር አስታውሰው መዘግየቱ ካልሆነ በስተቀር አሁን ውህደቱ መፈፀሙ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም ብለዋል፡፡ ውህደቱ እንደ አገር ለመቆም በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው ፕሮግራሞቹም ጥሩ ስለሆኑ አፈጻጸም ላይ ግን ድክመት እንዳይኖር በሚገባ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡ ለማህበረሰቡ ስለውህደቱና ስለፓርቲው የጠራ ግንዛቤ ለመፍጠር ትክክለኛውን ምስል መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡