አንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2030 እንደ ሀገራችን ደግሞ በ2023 ዓ/ም የወባ በሽታን ለማጥፋት በተያዘው ዕቅድ መሰረት ይህንኑ ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዳ ሀገር ዓቀፍ የወባ ሳምንት ዘመቻ በይፋ ተጀምሯል፡፡
የዘመቻውን መጀመር ይፋ ያደረጉት የከንቲባው የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ተወካይ አቶ መሃመድ አሚን እንደተናገሩት ‹‹በአስተዳደራችንም ይሁን እንደ ሀገር ያለውን የወባ በሽታ ስርጭት ለማስወገድ የሚረዱ ተግባራትን በተለያዩ ጊዜያት በሚካሄዱ ሥራዎች እንዲሁም ከአጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በሚከናወኑ ተግባራት የበሽታውን ስርጭት ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ባይቻልም በበሽታው የሚከሰተውን ህመምና ሞት በከፍተኛ ደረጃ መከላከል የተቻለ ሲሆን ይህንንም አጠናክሮ ለመቀጠል እንዲያስችል ወባን የማስወገድ ዘመቻ ንቅናቄ ሳምንት ዛሬ በይፋ መከፈቱን እያበሰርኩ በዚህ ዘመቻ የማህበረሰቡን ግንዛቤ በመጨመር፣ ለትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑ ቦታዎችን በማፅዳት፣ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በማፋሰስና በማዳረቅ፣ በኬሚካል የተነከሩ የአልጋ አጎበሮችን ዘወትር በመጠቀምና ላላስፈላጊ አገልግሎቶች ከመጠቀም በመቆጠብ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ እንድታበረክቱ አደራ እያልኩ ወባን በማጥፋት የአስተዳደራችንን ነዋሪ ጤናማ ለማድረግ ርብርብ ማድረግ አለብን›› ብለዋል፡፡
ከተሳታፊዎች በአስተዳደር ደረጃ ለወባትንኝ መራቢያነት ምክኒያት የሚሆኑ በከተማዋ ያላለቁ መንገዶች፣ ክፍት ቦዮች፣ ውሃ የሚያቁሩ መሬቶችና አስፓልቶችን በተመለከተ ጤና ቢሮ ከአስተዳደሩ ጋር ተነጋግሮ የጋራ መፍትሄ ሊፈልግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ኃለፊ ወ/ሮ ለምለም በዛብህ በበኩላቸው ለፋብሪካዎችና ለትላልቅ ሆቴሎች ፍቃድ ሲሰጥም ሆነ ከተሰጠ በኋላ ለወባ ትንኝ መራቢያነት ምክኒያት የሚሆኑ ፍሳሾችን በተመለከተ ክትትል መደረግ እንዳለበትና እስከ ዛሬ ወባን ለማጥፋት የተሰሩ ውጤታማ ሥራዎችን በተሻለ መነሳሳት ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረው ወባ ከሚከሰትባቸው ጊዜያት ቀደም ተብሎ የጥንቃቄ ስራዎችን በመስራት ወባን ለማጥፋት መረባረብ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡


