“የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ለመላው ሴቶች በርካታ መብቶች ና ነፃነቶችን ያጐናፀፈ ነው”። የድሬዳዋ አስተዳደር ሴቶች ህፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ጫልቱ ሁሴን

    በሴቶች ህፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አዘጋጅነት 17ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች ቀን “ህብረብሄራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ቃል፣ በተለያዩ ደማቅ ዝግጅቶች መላው ሴቶችን ያሳተፈ መድረክ በምክር ቤት አዳራሽ ተከብሮ ውሏል።

    በመድረኩም የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሴቶች ህፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ጫልቱ ሁሴን ሲገልጹ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዋናነት የብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መብት የተረጋገጠበት ህገ-መንግስት መሰረት በማድረግ ህገ መንግስቱ በጸደቀበት ህዳር 29 ቀን በየአመቱ የሚከበር ታላቅ በዓል መሆኑን ተናግረዋል:: የዚህን አመት የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል ስናከብርም በኢትዮጵያ መንግስት እና በህውሀት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ የተደረገውን የሰላም ስምምነት በስኬት በተጠናቀቀበት ማግስት መሆኑ በዓሉን ልዩ ገጽታንም ያላብሰዋል ብለዋል ፡፡

    ይህ የሰላም ስምምነት ለሀገራችን አዲስ ምእራፍ ከፋች ፣ለህዝቦቿ የሰላም ጸሀይን የሚያወጣ፣ሀገራችን ፊቷን ሙሉ ለሙሉ ወደ ልማት እንድታዞር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ የብሄር ብሀረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለመላው ሴቶችም በርካታ መብቶችን እና ነጻነቶችን ያጎናጸፈ ነው ያሉት ሀላፊዋ ሴቶች ከማጀት ወጥተው በኢኮኖሚ በማህበራዊ እና በፖለቲካ ተሳትፎ በማድረግ አንጸባራቂ ድሎችን የተጎናጸፉበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

    በአስተዳደሩም ለሴቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በተሰሩ ስራዎች ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ መቻሉንም ሀላፊዋ አንስተውል፡፡

    በቀጣይም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ቀን ለመላው ህዝቦች ያጎናጸሸፋቸውን ትሩፋቶች ፣የሴቶችን ሁለተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ማጎልበት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

    በመድረኩም የድሬደዋ ብልፅግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ሀላፊ በወ/ሮ ሁክሚያ መሀመድ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ማብራሪያ እና በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል፡፡