ይህንንም ምክንያት በማድረግ በዛሬው ዕለት በአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬክሽን ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።
በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ አብዱረህማን ሙሳ ሀገራችን የአካል ጉዳተኞችን ኮንቬንሽን መፈረሟን በመግለፅ ተግባራዊነታቸው ላይ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። አቶ አብዱረህማን አክለውም አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አለመሆኑንና በማንኛውም ሰው ላይ ሊያጋጥም የሚችል መሆኑን ተናግረዋል። ስለሆነም በሀገራችን ብሎም በከተማችን ድሬዳዋ የአካል ጉዳተኞችን መብት እንዲረጋገጥ በሁሉም መስክ አካል ጉዳተኞችን አሳታፊና አካታች ለማድረግ ሁሉም ማህበረሰብ የድርሻውን ሊወጣ ይገባዋል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በድሬዳዋ አስተዳደር አዘጋጅነት በሚካሄደው የአካል ጉዳተኞች ቀን ስነ-ስርዓት ላይ ለመታደም በሀገራችን ያሉ ባለስልጣናት፣ ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች፣ የተባበሩት መንግስታት ተወካዮች፣ የአፍሪካ ህብረት ተወካዮች ወደ ከተማችን እንደሚመጡም ገልፀዋል።
በመድረኩ የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ በሆኑት አቶ ሄኖክ ሰለሞን የአካል ጉዳተኞች መብት ምን ያህል ተግባራዊ እየተደረገ ነው እንዲሁም የኢትዮጲያ የአካል ጉዳተኞች መብትና የህግ ማዕቀፎቹ ምን ይመስላሉ? በሚል ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
በመድረኩ ተሳታፊ የሆኑ ዕንግዶችም ኢትዮጵያ በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ የፈረመችባቸውን ህጎች አሁን ላይ ወረቀት ከማድመቅ በዘለለ እየተተገበሩ እንዳልሆነ አንስተዋል። በተለይም በአብዛኞቹ ቢሮዎች አካባቢ ያሉት ህንፃዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆናቸውን ጠቅሰው አሳንሰር ቢሰራ አካል ጉዳተኞች ብቻ ሳይሆኑ አቅመ ደካሞችም የሚጠቀሙበት በመሆኑ ከዚህ በኋላ የሚገነቡት ህንፃዎች ይህንን ያማከለ እንዲሆን አሳስበዋል። ይህ በዓልም በከተማችን ድሬዳዋ መከበሩ የተለያዩ እንግዶች ወደ ከተማችን እንዲመጡ ስለሚጋብዝ ከተማችንን በቱሪዝሙ ገቢ እንደሚያስገኝ በማድረጉ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።
በውይይቱ መድረኩ የድሬዳዋ አስተዳደር ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ፣ የሲቪል ማህበራት፣ የአካል ጉዳተኞች ማህበር፣ ድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት፣ የፍትህ ተቋማት እንዲሁም ከሚዲያ አካላት የተጋበዙ እንግዶች ተገኝተዋል።
“አካል ጉዳተኞችን አሳታፊና አካታች ለማድረግ ሁሉም ማህበረሰብ የድርሻውን ሊወጣ ይገባዋል”። _ የድሬዳዋ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ሃላፊ ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓል ዘንድሮ በአስተዳደራችን ድሬዳዋ አዘጋጅነት “አካታች የፈጠራ ስራና ሽግግራዊ መፍትሔ ለኢትዮጲያ አካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተደራሽነት” በሚል መሪ ቃል ለ30ኛ ጊዜ ህዳር 24 ቀን 2015 ዓ.ም ይከበራል።


