ዓድዋ ተረት እንዳይመስልብን!

የዛሬ 128 ዓመት ዕለተ እሑድ በዓድዋ ተራሮች አናት የወጣች ፀሓይ ለዓለም ብርሃን ኾናለች፡፡ እነሆ ፀዳሏ እያበራ ከትውልድ ትውልድ በላቀ ድምቀት እየተዘከረም ይኖራል፡፡ ከብዙ ጥረትና ጥምረት በኋላ ኢትዮጵያውያን ያሳኩት የዓድዋ ድል የዓለምን የፖለቲካና ታሪክ ፈር የቀየረ ነው፡፡

ወቅቱ አውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች አፍሪካውያንን በባርነት ተናጋሪ እቃ አድርገዉ ከመገበያየትና ጉልበታቸዉን ወደ አውሮፓ ወስዶ ከመበዝበዝ ቀያቸዉን ተቆጣጥሮ የጥቍሮችን የተፈጥሮ ሀብት በጥቍሮች ጉልበት ለመዝረፍ ቅኝ ግዛትን እንደ ዐዲስ መከተል የያዙበት ነበር፡፡ ከበርሊን ኮንፈረንስ ማግሥት አፍሪካን ጠረጴዛ ላይ ተከፋፍለዉ ወደ አፍሪካ ሀገራት ቅኝ ገዢዎች ተስፋፍተው ነበር፡፡

በዚህ ወቅት ነበር ከቅኝ ገዥዎቹ አንዱ ጣሊያን ኢትዮጵያን በእጁ ለማስገባት ወደኢትዮጵያ በሰሜን በኩል የመጣው፡፡ የኢትዮጵያውያንን ጥንተ ታሪክ አጥንቶ የመጣዉ ጠላት በኃይል ኢትዮጵያን ለመያዝ እንደማይችል ገምቶ አሳሳች ስምምነቶችን በመፈጸም ነበር ግቡን ሊያሳካ የሞከረው፡፡ በዚህ መነሻነት የውጫሌ ውል በኢትዮጵያና ጣሊያን መካከል ተፈረመ፡፡ በ20 አንቀጾች የተከፋለዉ ውሎ የ17ኛዉ አንቀጽ የአማርኛና ጣሊያንኛ ትርጕም ለታቀደው ሴራ ማጠንጠኛ ነበር፡፡ የአማርኛዉ የውሉ ሐሳብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያከበረ ቢኾንም የጣሊያንኛዉ ግን ኢትዮጵያ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ስር እንደገባች የሚያረጋግጥ ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር ውል ለመዋዋል የግድ የጣሊያን ይሁንታ የሚያስፈልጋት ያደረገ ነበር፡፡

በዚህ ውል ሰበብ የኢትዮጵያና ጣሊያን ጦርነት መቀስቀሱ ግድ ኾነ፤ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ምታ ነጋሪት፣ ክተት ሠራዊት ብለው 12 የጦር መሪዎቻቸዉን አሰልፈዉ ወደ ግንባር ሊዘምቱ ጥሪ አስተላለፉ፡፡ በየአካባቢዉ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር በነበራቸዉ ልዩነት ሲዋጉ የነበሩ ነገሥታትና ባላባቶች ኹሉ ጠባቸዉን ጥለው “እኛ ነገ ይለይልናል፤ ዛሬ ሀገራችንን እናድን” ብለው ወደ ሰሜን ተመሙ፡፡ የእቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ ጥበብ የተሞላበት አመራር የመቀሌ ምሽግን በቀላሉ ማስለቀቅ አስቻለ፡፡ በላቀ ወኔና በራስ መተማመን የነበረዉ የኢትዮጵያ ጦር ዕለተ እሑድ ንጋት ላይ ደግሞ በወራሪዉ የጣሊያን ጦር ላይ የቁጣ ሰይፉን መዘዘ፡፡ የዓድዋ ተራሮች በጀግኖች ፉከራና ሽለላ፣ በፈረሶች ኮቴና ጩኸት፣ በሰይፍና ጎራዴ መፋጨትና ብልጭታ … ተናጡ፡፡ ከዐራቱም ማዕዘን የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን የዓድዋን ተራሮች ከጧቱ ጨረር ጋር ደም አስመሰሏቸው፡፡ ጀግኖች ዓድዋ ተራሮች ላይ በቀይ ደማቸዉና በነጭ ዐጥንታቸዉ አንፀባራቂዉን ዐዲስ ታሪክ ጻፉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ሰዎች ብቻ ሳይኾኑ ፈረሶች ጭምር ስለሀገር ክብር ተሠው፡፡

መሥዋዕትነታቸዉ ግን ደማቅ ታሪክ ጻፈ፤ የዓለምን የታሪክና ፖለቲካ አቅጣጫ የለወጠ ጀብድ ተፈጸመ፡፡ ኢትዮጵያውያን በሰዓታት ውስጥ የቅኝ ገዢዎችን ተስፋ አጨለሙት፤ በዓለም የታሪክና ፖለቲካ መዝገብ ላይ “የጥቍር ሕዝቦች ድል ተመዘገበ፤ ዓድዋ የመጀመሪያዉ የነጭ ኃይል የሽንፈት ቦታ!” ተባለ፡፡ በዚህ ታላቅ ድል ኢትዮጵያውያን ባላቸው ሙያ ኹሉ በዘመቻዉ ተሳትፈዋል፡፡ ሸማኔዎች የኢትዮጵያን ሰንደቅ እያመረቱ ለዐርበኞቹ በድል ጊዜ እንዲያውለበልቡ አቅርበዋል፤ የብረት ሥራ ባለሙያዎች ጦርና ጋሻ እየቀጠቀጡና ሰይፍ እየሳሉ ከዐርበኞቹ ዕኩል ዋጋ ከፍለዋል፤ አዝማሪዎች “ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ፤ መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ!” እያሉ ጀግኖችን ከጀግኖች እያፎካከሩ ወኔን ስለዋል፤ ወጌሻዎችና የባህል መድኃኒት ዐዋቂዎች ቁስለኞችን በጥበባቸዉ ፈውሰው ለድል አብቅተዋል …፡፡

በዓድዋ ድል የተመዘገበዉ ድል ላይ የእንስሳቱ አስተዋፅዖም ወደር የለሽ ነበር፡፡ ፈረሶች ዐርበኞችን ተሸክመዉ ከጠላት መካከል ተወርውረው እየገቡ መሥዋዕትነት ከፍለዋል፤ አህዮች፣ በቅሎዎችና ግመሎች ስንቅና ትጥቅ ተሸክመዉ ከደቡብ፣ ከምዕራብና ምሥራቅ ወደ ሰሜን ተምመዋል፡፡ ከብቶች፣ በጎችና ፍየሎች ከመላው ኢትዮጵያ ተነድተዉ ለዐድዋ ጀግኖች ስንቅ ተሠውተዋል፡፡

የዓድዋና አካባቢዉ ተራሮች በጠላት መድፍ ተበሳስተዋል፤ በጦርነቱ በአካባቢዉ የነበሩ ዕፅዋትና እንስሳት በእሳት ላንቃ ተለብልበዋል፤ የጠመንጃና ጎራዴ ሲሳይ ኾነዋል፡፡ ወንዞቹ በወዳጅም በጠላትም ደም ቀልተዋል፡፡ በአጠቃላይ ዓድዋ የኢትዮጵያ የኾኑ ሰዎች፣ እንስሳትና ተራሮች ዋጋ የከፈሉበት፣ በጋራ ታሪክ ከፍ ያለ የወል ታሪክ ነው፡፡ ይህ ዓለምን ያስደመመ ታሪክ ሰፈር ቀርቶ አህጉር አይመጥነውም፤ ከአፍሪካ አልፎ የካሪቢያንና የሌሎችም በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር የነበሩ ሕዝቦች የነፃነት ምልክትና ተስፋ ኾኗልና፤ የአብሮነትን ውጤት በእጅጉ አጉልቶ አሳይቷልና፡፡

የጋራ ድላችን የኾነው ዓድዋ በርካታ ትሩፋቶችን አስገኝቶልናል፡፡ ለአብነትም ብቸኛ በራሳችን ኅብረትና አንድነት ነፃነታችንን ያስጠበቅን ሕዝቦች አድርጎናል፡፡ አንድ የጦርነት ሕግና የሰብአዊ መብት ተቋም በዓለማቀፍ ደረጃ ባልነበረበት ምርኮኞችን በእንክብካቤ ይዘን በማቆየት ለነፃነታችን ዕውቅና እንደሰጡ በክብር እኛን ሊወጉ ያመጡትን መሣሪያ አስይዘን የምንሸኝ የሞራል ልዕልና ያለን ሕዝቦች መኾናችንን አስመስክረንበታል፡፡

በመላዉ ዓለም የነበሩ የነፃነት ትግሎች እንዲቀጣጠሉ አነሣሽ ኃይል ነበርን፡፡ በዓለማቀፍ ተቋማት ውስጥ ብቸኛ የጥቍር ሕዝቦች ወኪሎች አድርጎናል፡፡ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ተቋማትን በመመሥረት ረገድ ጉልህ ሚና መጫዎት የሚያስችል ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ዐቅም ፈጥሮልናል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የግል ፍላጎትና ግጭትን በመተዉ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የማያወላውሉ ተከታታይ ትውልዶች እንዲኖሩን ምክንያት ኾኖናል፡፡

ይሁን እንጅ ግዙፉ ዓድዋ የሚመጥነዉ መታሰቢያ ሳያገኝ ለዘመናት ኖረ፡፡ ከበርካታ ቁጭት የሚያጭሩ ዓመታት በኋላ በለውጡ መንግሥት መሠረቱ የተቀመጠዉ የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚዬም በ128 ዓመት ለምረቃ በቅቷል፡፡ የጋራ ታሪካችን በኾነው የዓድዋ ድል ምክንያት የተገኘዉ ሙዚዬሙ የጋራ ቅርሳችን ኾኖ መዲናችንን አደመቀ፡፡ ከየአቅጣጫዉ የዘመቱ የዓድዋ ሰማዕታትን በሚመጥናቸዉ ከፍታ ዘከረልን፡፡

አሁንም ዓድዋን መሰል ጀብድ የሚጠይቁን አጀንዳዎች አሉን፡፡ የውስጥ ጠባችንን ጥለን፣ የሀገር ፍላጎትን ከየግል ፍላጎታችን አልቀን፣ ዕድሜ፣ ፆታ፣ ሃይማኖት፣ የዘር ሐረግ፣ የፖለቲካ አስተሳሰብ … ሳይለያዩን ለላቀ ክብርና ከፍታ በኅብረት መቆም አለብን፡፡ ነፃ የተረከብናትን ሀገር በነፃነት የማስረከብ ኃላፊነት አለብንና፡፡ ለሌሎች የምትረዳ ሀገር ቀደምቶቻችን አውርሰውን ነበር፤ ነገር ግን በትብብርና በትጋት ሳንሠራ ዘመናትን አሳለፍንና የተቀቀለ ስንዴ ምፅዓተኞች ኾንን፡፡ በዓድዋ ድል አንገት ባስደፋናቸዉ ጠላቶቻችን ፊት አንገት ደፍተን ስንዴ ተመፅዋች ኾንን፡፡ ይህንን አዳፋ ታሪካችንን ለመፋቅ በኅብረት ቀን ከሌት መሥራት አለብን፡፡ ከየአቅጣጫዉ ተሰባስበን በዓድዋ የተዋደቁ ጀግኖች ልጆች በከፋፋይ አጀንዳ ተወስደን እርስ በርስ ስንጋደል የዓድዋ ድል ተረት ተረት መሰለብን፡፡ ዓድዋን እየዘከርንና ወደከፍታችን እያየን ጠባችንን ልንተውና ልንተባበር ይገባል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *