አረንጓዴ ልማት ዘመቻውን ህብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲመራው የመገናኛ ብዙሃን የጀመሯቸውን ውጤታማ ተግባራት ማጠናከር አለባቸው

የመገናኛ ብዙሃን የአረንጓዴ ልማት ዘመቻውን ለህብረተሰቡ በማስረፅ በባለቤትነት እንዲመራው የጀመሯቸውን ውጤታማ ተግባራት የበለጠ ማጠናከር እንዳለባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ ገለጹ።

“አረንጓዴ ልማት ለዘላቂ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ ኢዜአ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት ተጠናቋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ በፓናል ውይይቱ ማጠናቀቂያ ወቅት፤ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመዘርጋት ከተፈጥሮ ጋር የሚስማማ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ ተናግረዋል።

እነዚህ ተግባራት የኢትዮጵያን ከፍታ እና ብልጽግና በማረጋገጥ በኩል ወሳኝ ሚና እያበረከቱ ይገኛሉም ብለዋል።

ይህን የአረንጓዴ ልማት ዘመቻ ለህብረተሰቡ በማስረፅ በባለቤትነት እንዲመራው የመገናኛ ብዙሃን የጀመሯቸውን ውጤታማ ተግባራት የበለጠ ማጠናከር እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የአረንጓዴ ልማት ስራ በየደረጃው በህብረተሰቡ ውስጥ እየሰረጸ መምጣቱንም ተናግረዋል።

መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት እያከናወነች ያለችውን ተምሳሌታዊ ስራ በማሳየት የበለጠ ውጤት እንዲመዝገብ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አጽንኦት ሰጥተውታል።

የድሬዳዋ አስተዳደር በአረንጓዴ ልማት ላይ ያከናወነው ስራ አበረታች መሆኑንና ለአካባቢ ጥበቃ ተግባራት ጉልህ ሚና እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህ ስራዎችም በአስተዳደሩ ቀደም ሲል ይከሰት የነበረውን የጎርፍ አደጋ በመቀነስ ተጨባጭ ውጤቶችን መመዝገባቸውን ነው ያመለከቱት።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተለይ በአረንጓዴ አሻራ እና በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ እየተመዘገቡ የሚገኙት ተጨባጭ ውጤቶች ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች የማይበገር ማህበረሰብና ኢኮኖሚ ለመፍጠር የተጀመረውን ጥረት እያሳኩ መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህ የተመዘገቡ ጅምር ስራዎች ኢትዮዽያ በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ ለአለም እያስተማረች መሆኑን አመላካች ናቸው ብለዋል።

በአገሪቱ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን በእውቀት ላይ የተመሰረተ ጥልቅ የሆኑ የመረጃ ማሰራጨት ስራቸውን የበለጠ በማጠናከር መተግበር እንዳለባቸው አመላክተዋል።

በተለይ ኢዜአ መረጃን ለህዝብ ከማቅረብ በዘለለ የአረንጓዴ ልማት ዘመቻው ህዝባዊ አጀንዳ እንዲሆን እያከናወነ የሚገኘው ስራ በዓርዓያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *