በድሬዳዋ ከተማ አሸዋ የገበያ ስፍራ በተከሰተው የእሳት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን የንግዱን ማህበረሰብ በርብርብ መልሶ ለማቀዋቋም የሚያስችል ሀብት የማሰባሰብ ስራ መጀመሩን የድሬደዋ አስተዳደር ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉካ መሀመድ በዛሬው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ወ/ሮ ሙሉካ የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱን በመጠቆም፤ አራት ባንኮች ላይ ድጋፍ የሚሰበሰብበት ብሎክ አካውንት እንደተከፈተና የጉዳቱ መጠን ተለይቶ የተሰበሰበው ሀብት መልሶ ማህበረሰቡን ለማቋቋም እንደሚውል ገልፀዋል።
በቀጣይም ለማህበረሰቡ በሚመች አማራጭ የድጋፉ ሁኔታ እንደሚመቻች የገለፁት ሀላፊዋ በአይነትም ድጋፍ ማረግ ለማሚፈልጉ ማህበረሰቦች የተለያዩ መጋዘኖች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
ጉዳዩ ጊዜ የማይሰጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የድሬደዋ ነዋሪዎች እንዲሁም በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም የሚኖሩ የድሬደዋ ወዳጆችና ተወላጆች እንዲሁም አጎራባች ክልሎችና መላው የኢትዮጲያ ህዝብ የአቅሙን ድጋፍ እንዲያደርግና ለጉዳት የተዳረጉትን ማህበረሰብ መልሶ በማቋቋም የበኩላቸውን እንዲወጡ ወ/ሮ ሙሉካ ጥሪ አቅርበዋል
የወረዳ 07 አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብዱረዛቅ መሀመድ እና ጉዳት የደረሰባቸውን ማህበረሰብ በመወከል በመግለጫው የተሳተፉት ማህበረሰቦችም በበኩላቸው በተከፈቱት አካውንቶች ድጋፍ በማድረግ ሁሉም ማህበረሰብ ከጎናችን እንዲቆም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡


