ተደራሽነቱን በማስፋትና የአባል ቁጥሩን በማብዛት ተፎካካሪ ለመሆን እንደሚሰራ የኛ የገንዘብ ቁጠባ እና ብድር ህብረት ስራ ማህበር ገለፀ ።

ማህበሩ 2ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤዉን አካሂዷል። በጉባኤው የማህበሩ 2016 ዓም የስራ አፈፃፀም ፣ የኦዲት ሪፖርት እንዲሁም የ2017 ዓ.ም እቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በ2016 ዓ.ም ከ76 ሚሊየን ብር በላይ ለአባላቱ በብድር ያስተላለፈ ሲሆን ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን ፣ከአምስት ሚሊየን ብር በላይ በተለያዩ መንገዶች ገቢ መገኘቱን ፣ አጠቃላይ የሃብት መጠኑም 77 ሚሊየን ብር በላይ መደርሱ ተገልፃል።

ምንም እንኳን ህብረት ስራ ማህበሩ ተቋቁሞ ስራ ከጀመረ በጣም በአጭር ጊዜ ያከናወናቸው ሰራዎች አበረታች ቢሆኑም በተለይም የማህበሩን ትርፋማነት ከማሳደግ አንፃር የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃና መጠን ማስፋት፣የአባለት ቁጥርን ማሳደግ፣ ዘላቂነትና አዋጭነታቸው የተጠና የብድር አገልግሎቶችን አጥንቶ መተግበር፣ከብድር አመላለስ ጋር የጎላ ችግር እንዳይፈጠር የሚያስችሉ የተጠናከረ የክትትል ስራ መከናወን አንደሚገባ በጉባኤው በተደረገ ውይይት ተመላክቷል።

ማህበሩ አገልግሎት ሰጪ ከመሆኑ አንፃር ለነባር አባላትም ሆነ አዲስ ወደ ማህበሩ ለመቀላቀል የሚፈልጉ ሰዎችን በቀላሉ ለመድረስ እንዲቻል የአገልግሎት መስጫ ማእከላቱን ማስፋት እንዳለበት እንዲሁም ከሌሎች አጋር አካላት ጋር ያልውን የስራ ትስስር ማጠናከር እንደሚገባ በጉባኤው ከአባላት በስፋት ተነስቷል።

የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ዳንኤል ታደሰ በጉባኤው የተቋሙን የወደፊት የስኬት ጉዞ ለማቃናት የሚያስችሉ የሃሳብ ግብአቶች መገኝት መቻሉን ገልፀዋል።በቀጣይ ከአባላት የተነሱ ሃሳቦችን እንዲሁም በእቅድ የተያዙ ስራዎችን በመመስረት ከአሰራር ፣አደረጃጀት፣ ከተጠያቂነትና ከህግ ማዕቀፍች ጋር የተያያዙ ሰፊ ሰራዎች ተፈፃሚ ለማድረግ እንቅስቃሴ አንደሚደረግ አስረድተዋል።

በአገልግሎት እረገድም አሁን አየሰጣቸው ከሚገኙ መደበኛ የብድርና ቁጠባ በተጨማሪ ከግብርና /በተለይ የከተማ ግብርና/ እንዲሁም የሊዝ ፋይናንስ አቅርቦቶችን ለማድረስ መታቀዱን አቶ ዳንኤል ጠቁመዋል።የማህበሩን የሃብት መጠን ከፍ ለማድረግ በዘርፉ ከሚሰሩ አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ስራዎች እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል።

የድሬደዋ የህብረት ስራ ማህበራት ማደራጃ ፅ/ቤት ተወካይ አቶ ሱልጣን አሚሶ የህብረት ስራ ማህበራት የፋይናንስ እጥረትን ለመከላከል አማራጭ አቅም በመሆን የህብረተሰቡን ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ የቁጠባ ባህልን በማሳደግ አባለት ሃብት እንዲያፈሩ ከማስቻል አኳያ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ገልፀዋል።

ጠንካራ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት የሚያበረክቱት አስተዋፆ ያለውን ጠቀሜታ በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ መንገዶች ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ መሰል ማህበራት ተሞክሮ መረዳት እንደሚቻል አቶ ሱልጣን ገልፀዋል።

የኛ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር ባለው አጭር የስራ ጊዜ ያስመዘገበው ውጤት ተስፋ የሚጣልበት እንደሆነ የገለፁ ሲሆን ወደፊት መልካም ተሞክሮዎቹን በማስፋትና ያሉበት ክፍተቶች በመቅረፍ ለበለጠ ውጤት መስራት እንደሚገባው ጠቁመዋል።

በጉባኤው የቀረበው የማህበሩ 2016 ዓም የስራ አፈፃፀምና የኦዲት ሪፖርት በአባላት ሙሉ ድምፅ የፀደቀ ሲሆን በተጓደሉ የስራ አስፈፃሚ አባላትና የቁጥጥር ኮሚቴ አባላት ምርጫ እንዲሁም አምስት የተጠባባቂ የኮሚቴ አባላት ምርጫ ተከካሂዷል።

ማህበሩ በአሁን ሰአት ከ1,400 በላይ አባላትን አቅፎ ይገኛል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *