ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በድሬዳዋ የተመለከቷቸው የሥርዓተ ምግብ፣ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን፣ የልማት ትሩፋት እና የነፃ የንግድ ቀጣና ሥራዎች የተሳሰረ የልማት ፓኬጅ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በጉብኝታቸው በሥርዓተ ምግብ መርሐ ግብር ተጠቃሚ የሆኑ ነዋሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በምግብ ራሳቸውን መቻላቸውን እንዲሁም ልጆቻቸውም የተመጣጠነ ምግብ እያገኙ እንደሆነ ማየታቸውንም አመልክተዋል።
በማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሥርዓት የተጀመሩ ሥራዎችም የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።
“በከተማ ግብርና እና የሌማት ትሩፋትም በቂ የወተት፣ የእንቁላል እና የማር ውጤቶችን በማምረት የመቀንጨር ችግርን ለመቅረፍ የሚያስችሉ እና ገበያውን የሚያረጋጉ ሥራዎችን ተመልክተናል” በማለት የመርሐ ግብሩን ውጤታማነት አረጋግጠዋል።
አክለውም “ሌላው በጉብኝታችን የተመለከትነው የነፃ የንግድ ቀጣና በማምረቻ ኢንዱስትሪ እንዲሁም በገቢና ወጭ ንግድ ማዕከል የሚያደርገን ሲሆን፤ ለኤክስፖርት ብቻ ሳይሆን ተኪ ምርት ላይም ትልቅ አስተዋፅዖ የሚያበረክት ነው” ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፥ “በተናበበ እና በተሳሰረ መልኩ በትጋት ከሠራን የበለፀገ ሀገር እና ማኅበረሰብ በመፍጠር ምሳሌ የመሆን ጉዟችን በአጭር ጊዜ እንደሚሳካ” በጉብኝቱ ከተመለቷቸው ሥራዎች መረዳታቸውን ገልጸዋል።


