#DGC መስከረም 9 /2016
የድሬዳዋ ናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የትምህርት መማሪያ ቁሳቁሶችን በዛሬው እለት በገጠር እና በከተማ ለሚገኙ አስራ አንድ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ድጋፍ አድርጓል፡፡
የናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር ስራ አስፈፃሚ ሚስተር ሊኡ ጄሽንግ በድጋፍ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ፋብሪካው አገር ከመገንባት ባሻገር የትምህርቱን ዘርፍ ለማገዝና ለመደገፍ በላቀ ቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አቡበከር አብዶሽ ባስተላለፉት መልዕክት በአስተዳደሩ ስር የሚገኙ ተቋማት የትምህርት ዘርፉን መጠናከር ለማሳካት እያደረጉ የሚገኙት ድጋፍ አበረታች እንደሆነ ጠቁመው፤ ድጋፍና እገዛው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልፀዋል፡፡
የናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር ምክትል ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ቢፍቱ መሐመድ (ዶ/ር) እንደተናገሩት ናሽናል ሲሚንቶ ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፈጠረው የስራ ዕድል በተጨማሪ አገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት በሚደረገው ተግባራት ላይ በትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ በትምህርት ቤቶች ላይ ምገባ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት የመገንባት፣ እንዲሁም የማዕድ ማጋራት ላይ በመሳተፍ ድርጅቱ ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ ናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ የተገዙ የትምህርት መማሪያ ደብተር፣ እስክሪብቶ፣ እርሳስ፣ የመማሪያ ቦርሳ ለ11 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በደገፉበት ስነ ስርዓት ላይ የወረዳ አራት የስራ ኃላፊዎች፣ የተማሪ ወላጆች፣ ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡
የተማሪ ወላጆች እና ተማሪዎች ናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማህበር ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው፤ ተማሪዎቹ የላቀ ውጤት ለማምጣት በርትተው እደሚያጠኑ ገልፀውልናል፡፡


