#DGC መስከረም 8/2016
በዛሬው ዕለት ከኢጋድ፣ ከወርልድ ባንክና ከኢ.ፌ.ድ.ሪ ግብርና ሚኒስተር የተውጣጣው ልኡካን ቡድን በድሬዳዋ አስተዳደር ገጠር ቀበሌዎች በምግብ ስርአት ማጠናከሪያ ፕሮግራም /በኤፍ ኤስ አር ፒ / የተሰሩ ስራዎችን ከአስተዳደሩ አመራሮችንና ከሚመለታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል፡፡
በጉብኝቱም በሁሉ ሞጆ፣ በዱጁማ በኢጃናኒና በገንደ ሬጌ ገጠር ቀበሌዎች በመስኖ ልማትና በወንዝ ጠለፋ፣ በመስኖ ካናል ፕሮጀክት የተሰሩ ስራዎችን እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ እርሻዎችንና የዶሮ እርባታ ስራችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት ያነጋገርናቸው የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ፣ ማእድን ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የኃላፊ ተወካይ አቶ መሀመድ አሚን በአስተዳደሩ በመስኖ ልማት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ አርሶ አደሩም በተለምዶ ከሚያለማው ከማሽላና ከበቆሎ ወደ አትክልትና ፍራፍሬ በመግባት አበረታች ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተናገረዋል፡፡
የምግብ ስርአት ማጠናከሪያ ፕሮግራም /ኤፍ ኤስ አር ፒ /ፕሮጀክት የድሬዳዋ ማናጀር አቶ ስሻው አያሌው በበኩላቸው ቡድኑ ወደ ድሬዳዋ በመምጣት ስራዎችን ተዘዋውሮ በመጎብኘቱ አመስግነው፤ በጉብኝቱም በፕሮጀክቱ በተሰሩ ስራዎች አርሶ አደሩ በተጨባጭ እየተጠቀመ መሆኑን መመልከታቸውን ገልፀዋል፡፡፡
በድሬዳዋ በተለይም በመስኖ ልማት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ወንዝን ጠልፎ በማልበማትና በዶሮ እርባታው ዘርፍ አበረታችና ይበል የሚያስበሉ ስራዎች መሰራታቸውን የገለጹት ደግሞ በጉብኝቱ ወቅት ያነጋገርናቸው የልኡክ ቡድኑ አባላት ናቸው፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ አያይዘውም ድሬዳዋ ላይ ስራዎች በህብረተሰብ ተሳትፎ በርብርብና በቅንጀት በመሰራቱ የአርሶ አደሩ ህይወት እንደተቀየረና ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ ነው ሲሉ ተናገረዋል፡፡


