በድሬዳዋ አስተዳደር በጉጉባ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት 5 መቶ ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የተማሪዎች ምገባ ፕሮጀክት ሊጀመር ነው

ኤልኔት ፋውንዴሽን ከድሬዳዋ ልማት ማህበር እና ከድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን 5 መቶ ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና በድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኘው በጉጉባ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የሚተገበር የተማሪዎች ምገባ ፕሮጀክት ለማስጀመር የፊርማ ስነ-ስርአት በዛሬው ዕለት አካሄደ፡፡

በመርሀ ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አሊዪ እንደ ሀገር የደረሰብንን የትምህርት ስብራት ለመጠገን የምገባ ፕሮግራም ከፍተኛ አሰተዋፆ እንዳለው ገልፀው፤ የተማሪዎች ምገባ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ተማሪዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ከማገዙ በተጨማሪ የተማሪዎችን የመጠነ ማቋረጥ በመቀነስ ተመሪዎች የተመጣጠነ ምግብ አግኝተው ትምህርታቸውን በነቃ መልኩ እንዲከታተሉ እንደሚያስችል ተናገረዋል፡፡

በመጨረሻም አቶ ሱልጣን ኤልኔት ፋውንዴሽንን በማመስገን በቀጣይም ይህ አይነቱ ትውልድን የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የድሬዳዋ ልማት ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ከተማ ተሰማ በበኩላቸው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች በምግብ እጥረት የተነሳ ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ይህ የምገባ ፕሮግራም ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለው አመላክተዋል፡፡

የኤልኔት ፋውንዴሽን የፕሮግራም ዳይሬክተር ዶ/ር ራሄል ጂጊ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ለአንድ አመት የሚቆይ መሆኑን በመጠቆም በቀጣይም ፕሮጀክቱን ለማስቀጠል በርብርብና በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *