ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦችን ህይወት በዘላቂነት ለማሻሻል በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለፀ

በድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን በወረዳ 6 እና በወረዳ 9 እየተተገበረ የሚገኝውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት ማቋቋሚያ ( EAC ) ፕሮጀክት ከባለድረሻ አካላት ጋር የመግባቢያ ሰነድ የፊርማ ስነስረት ተካሂዷል።

ባለስልጣኑ የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራረመው ከድሬ ማይክሮ ፋይናንስና ከኢትዮ ኢጣሊ ፖሊቴልኒክ ኮሌጅ ጋር ነው።

በስነ-ስረአቱ ላይ በድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ስራ አስኪሃጅ አቶ አብዱ መሃመድ በፕሮጀክቱ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦችን በመረጡት የስራ ዘርፍ እንዲሰማሩ የሚያስችል ድጋፍ ማድረግን ጨምሮ አካባቢን መጠበቅ መሰረት ያደረጉ ተግባራትን በስፈታ እየተከናወኑ በአጭር ጊዜ ውስጥም ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል።

በተለይም ደግሞ ፕሮጀክቱ በአብዛኛው ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን የገለፁት ስራ አስኪሃጁ ሰው ተኮር የሆኑ ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል ።

በፕሮጀክቱ የሚከናወኑ ስራዎች የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት የግድ እንደሚል ከድሬ ማይክሮ ፋይናንስና ከኢትዮ ኢጣሊ ፖሊቴልኒክ ኮሌጅ ጋር አብሮ ለመስራት የተደረገው የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ በቴክኖሎጂ የተደገፉ ስራዎችን ለማከናወን ብሎም ያለን የፋይናንስ አቅም በአግባቡ ስራ ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ስራዎችን ለማከናወን እንደሚረዳ አቶ አብዱ ገልፀዋል ።

የድሬደዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የማህበረሰቦች የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት መቋቋም ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ በላይነህ ደስታ በዚህ ፕሮጀክት አማካኝነት የሚደገፉ ዜጎች 14ሺህ በላይ የሆኑ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ በአራት ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ሲሆን ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ መስጠት ፣የጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን ጥገና ማከናወን ፣የጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦችን የኑሮ ማሻሻያ ድጋፍ ማድረግ ስማርት የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ የጎርፍ ተጋላጭነት መቀነስ መሆናቸውን አቶ በላይ ገልፀዋል።

ባለስልጣኑ በፕሮጀክቱ እነዚህ ስራዎችን ሲያከናውን የሚያደርገውን ጥረት የበለጠ ሙሉ ለማድረግ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መቀናጀት እንደሚገባ ታሳቢ በማድረግ ከድሬ ማይክሮ ፋይናንስና ከኢትዮ ኢጣሊ ፖሊቴልኒክ ኮሌጅ ጋር በጋራ ለመስራት ከስምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

የድሬ ማይክሮ ፋይናንስና የኢትዮ ኢጣሊ ፖሊቴልኒክ ኮሌጅ ወክለው የተገኙ የስራ ሃላፊዎች በበኩላቸው ተቋማቱ ዋና ተግባራቸው የማህበደቡን ችግር የሚፈቱ ስራዎችን ማከናወን እንደመሆኑ ከባለስልጣኑጋር በጋራ ለመስራትና የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን በወረዳ 6 እና በወረዳ 9 እየተተገበረ የሚገኝውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት ማቋቋሚያ ( EAC ) ፕሮጀክት ለቀጣይ አምስት አመታት የሚዘልቅ መሆኑ ታውቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *