በአስተዳደሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበረውን የሰላም ቀን አከባበርን አስመልክቶ ከተለያዩ የሀይማኖት ተቋማት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ።
ውይይቱ በዋናነት ድሬዳዋ የሰላም ቀጠና በመሆን ለሀገራችን ብሎም ለዓለም ተምሳሌትነትን ያሳየችበት ከተማ በመሆኑ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የፊታችን ታህሳስ 12 ቀን “ሀይማኖቶች ለሰላም እና ለአብሮነት“ በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበረውን የሰላም ቀን በአስተዳደሩ በደማቅ መርሀ ግብር ለማክበር ከወዲሁ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ እንደሆነ ተገልጿል።
በዓሉም በተለያዩ መርሀ ግብሮች እንደሚከበር የገለጹት የድሬዳዋ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ የሆኑት ሼክ ኢብራሂም ኢማም እንዳሉት የሰላም ቀን ለማክበር የኢትዮጲያ የሀይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ ከፌደራል እና ከክልል የሚመጡ የሀይማኖት ተቋማት ተወካይና የሰላም ቢሮ ተጠሪዎች ፣የፍትህ አካላት፣ ተጋባዥ እንግዶች እንዲሁም በርካታ የአስተዳደሩ ነዋሪዎች የሚገኙበት ሲሆን በእለቱም በድሬድዋ አለም አቀፍ ስቴዲየም የሀይማኖት አባቶች ለሀገር ሰላም ዱዓ የሚያደርጉበት የሚጸልዩበት የሚባርኩበት እንዲሁም በሰላም እሴት ግንባታ ዙሪያ የፓናል ውይይቶች እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በበዓሉ በአስተዳደሩ ያለውን ሰላም እውቅና የመስጠት መርሀግብር እንደሚኖር እንዲሁም የተፈጠረውን ሰላም በማጽናት በኩልም የአስተዳደሩ ነዋሪዎች፣ ወጣቶች ድርሻቸው ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም አካላት ከሀይማኖት ተቋማት እና ከአስተዳደሩ ጋር በመሆን ሊሰሩ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡
በዓሉንም ለማክበር የሚመጡ ተሳታፊ እንግዶችን በመቀበል እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎቶችን በማቅረብ በኩልም ዝግጅት መጠናቀቁም ተገልጿል፡፡


