በዚህም በስፓርት ኮምሽን ሁለ-ገብ ሜዳ የድሬዳዋ ከፍተኛ አመራሮች፣ ቤተሰቦቹ፣ የሙያ አጋሮቹ እና የድሬደዋ ነዋሪዎች በተገኙበት የስንብት መርሐ-ግብር በማከናወን በእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን የቀብር ስነ ስርዓታቸው ተፈፅሟል።
በሽኝት ስነ-ስርአቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በዶ/ር አቤል መልካሙ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን የገለፁ ሲሆን፤ ዶ/ር አቤል ትንሽ ትልቁን አክባሪ፣ ስራ ወዳድና ህዝባቸውን አገልጋይ የነበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ክቡር ከንቲባ ከድር አያይዘውም ከ ዶ/ር አቤል የምንማራቸው በርካታ ቁም-ነገሮች እንዳሉ ጠቁመዋል።
ዶክተር አቤል ድሬዳዋን ከልቡ ወዳጅና ህዝቧንም በሙያው ጨምሮ ባለው ነገር ሁሉ ሲጠቅም የኖረ ባለውለታ መሆን ከንቲባ ከድር ተናግረው ይህን ደግ ሰው በማጣታችን ሀዘናችን ጥልቅ ነው በማለት ለመላው የድሬዳዋ ህዝብ መፅናናትን ተመኝተዋል።
ዶ/ር አቤል ሁሌም በልባችን ይኖራል፤ሁሌም እንዲታወስ ደግሞ በስሙም ጤና ጣቢያ እንደሚሰየም ክቡር ከንቲባ ከድር አመላክተዋል።
በመጨረሻም ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ሁሉም ማህበረሰብ በየተሰማራበት ሞያ ሁሉ የዶ/ር አቤልን በጎ ተግባር በአርአያነት በመከተል ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ የሆኑት ዶ/ር ፅጌሬዳ ክፍሌ በበኩላቸው ዶ/ር አቤል በስራ አጋጣሚ ያገኛቸውን ታማሚዎች ሁሉ እንደ ቤተሰብ የሚያቀርብና ያለውን ለወገኖቹ አካፎሎ የኖረ ዶክተር መሆኑን ገልፀው፤ በህልፈተ ህይወቱ ልባችን ተሰብሯል በማለት ለሁላችን መፅናናት ይስጠን በማለት ተናግረዋል።
በኤደን ሳሙኤል
ፎቶ:- አገኘሁ ሸዋረጋ


