የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን ባስተላለፉት መልዕክት ሙስና የአስተዳደር ስርዓትን የሚሸረሽር፣ የህዝብ አመኔታን የሚንድ እና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትን የሚያደናቅፍ መሆኑን አንስተዋል፡፡
21ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ=ሙስና ቀን ‘”ከወጣቶች ጋር በመተባበር ሙስናን መከላከል፤ የነገን ስብዕና ለመቅረጽ“ በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ሲሆን መሪ ቃሉ ለበዓሉ የተመረጠበት ምክንያት ሙስና ያለልዩነት ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን የሚጎዳ፣ ውስብስብ፣ ድንበር ተሻጋሪ እና ዓለም አቀፍ ችግር መሆኑን በመገንዘብ የጋራ ጠላት የሆነውን ሙስና በጋራ መከላከል በማስፈለጉ እንደሆነ አቶ ገበየሁ ተናግረዋል፡፡
አለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀንን ስናከብር ሙስናን በመከላከል ረገድ ወሳኝ እርምጃ በመሆኑ ሁሉንም መልካም አስተዳደርን የሚያጎለብት የአቋም ባህል በማዳበር የስነ-ምግባር አገልግሎት አሰጣጥን አስፈላጊነት በመገንዘብ እንዲሆን አሳስበዋል፡፡
ፍትሃዊ የአገልግሎት አሰጣጥና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ላይ እንቅፋት በመፍጠር ጉቦ፣ ምዝበራ እና ወገንተኝነትን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች የሚታይ ሲሆን የሙስና ተጽእኖ ጥልቅ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ሙስና የሚመነጨው ከስነ ምግባር ዝቅጠት፣ ከታማኝነት ጉድለት፣ ከግልፀኝነት መጥፋት፣ ከአሰራር ስርዓት መጓደል እንደሆነ የገለፁት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር የስነ- ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ፌኑስ አብዱጀባር ናቸው፡፡
ሀገር እንዳያድግ ቀልጣፋና ግልፀኝነት ያለው የአሰራር ስርዓት እንዳይኖር የሚያደርገው ሌብነት ነው፤ ሌብነትን መከላከልና መቀነስ የሚቻለው ከራስ ነው የሚጀምረው ያሉት አቶ ፌኑስ የመንግስት ተሿሚው ሆነ ባለሞያው ተገልጋዩን የህብረተሰብ ክፍል አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት በተቀመጠው የአሰራር ስርዓትና በህግና ደንብ ብቻ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር የስነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በአራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በማተኮር ሰፊውን ባለድርሻ አካል በማሳተፍ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የተገለፀ ሲሆን፣ በወረዳ፣ በገጠር ክላስተር፣ በሴክተር ተቋማት ያሉ አመራሮችና ባለሞያዎችን፣ እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሰራቱ ተነግሯል፡፡
የሙስና ጉዳቱን በመገንዘብ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥቆማዎች እንደሚደርሳቸው የተናገሩት አቶ ፌኑስ በ2016 ዓ.ም ብቻ የጥቆማ ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ ሃምሳ ስድስት ሚሊዮን ብር እንዲተርፍ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አቶ ገበየሁ ጥላሁን፣ የድሬዳዋ አስተዳደር የህዝብ ቅሬታና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ እና የከንቲባ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ሰአዳ አዋሌ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር የስነ- ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ፌኑስ አብዱጀባር፣ እንዲሁም የከንቲባ ጽ/ቤትና ተጠሪ ተቋሟት አመራሮች እና የከንቲባ ጽ/ቤትና ተጠሪ ተቋሟት ሰራተኞች በመድረኩ የተገኙ ሲሆን በመድረኩም የጥያቄና መልስ ውድድርና በሙስና ዙሪያ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጓበታል፡፡
በበድሉ ኃይሌ
ምስል፡- ሰላም አበበ


