“ሄር ኢሴ” ግጭት አፈታት በማህበረሰቡ ውስጥ የሚነሱ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ከመቻሉም በላይ ከሌሎች ህዝቦች ጋር ለዘመናት ተቻችሎና አብሮ በመኖሩ ለዘመናዊ ፍርድ ሂደትም የራሱ የሆነ የጎላ ሚና እንዳለው ተገለፀ::

በ19ኛው የዩኒስኮ ጉባኤ ላይ በመሳተፍ “ሄር ኢሴ” የሶማሌ ኢሣ ማህበረሰብ ያልተጻፈ ባሕላዊ ሕግ በሰው ልጆች ወካይ ዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስነት ያስመዘገበው ልዑካን ቡድን በዛሬው ዕለት ጠዋት ወደ ድሬዳዋ መግባቱን ተከትሎ በኡጋዝ ሙስጠፌ መሀመድ ቤት ደማቅ የአቀባበል መርሀ ግብር ተከናውኖለታል።

በዚህም በመድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) “ሄር ኢሴ” የሶማሌ ኢሣ ማኅበረሰብ ያልተጻፈ ባሕላዊ ሕግን በሰው ልጆች ወካይ ዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስነት በመመዝገቡ የተሰማቸውን ደስታ በመግለፅ፤ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።

“ሄር ኢሴ” ለበርካታ አመታት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ አሁን ላይ በመድረሱ ጠብቀው ያቆዩልንን አባቶችን እንዲሁም በቅርስነት እንዲመዘገብ የበኩላቸውን ድርሻ ለተወጡ አካላትም ክቡር ከንቲባ ከድር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢሳ ማህበረሰብ ያልተፃፈ ባህላዊ ህግ ተጠብቆና የሚገባውን ክብር አግኝቶ በቅርስነት እንዲያዝ በኢትዮጵያ አስተባባሪነት ኢትዮጵያ ፣ ጅቡቲና ሶማልያ በጋራ ያዘጋጁት ሰነድ በአፍሪካ የመጀመሪያው ሶስት የምስራቅ ቀንድ የአፍሪካ ጎረቤት ሀገራት ያስተሳሰረና ለስኬት የበቃ አኩሪ ታሪክ መሆኑንም ከንቲባ ከድር ጠቁመዋል።

በሄር ኢሴ ግጭት አፈታት በማህበረሰቡ ውስጥ የሚነሱ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ከመቻሉ በላይ ከሌሎች ህዝቦች ጋር ለዘመናት ተቻችሎና አብሮ በመኖሩ ለዘመናዊ ፍርድ ሂደት የራሱ የሆነ የጎላ ሚና እንዳለው ክቡር ከንቲባው ገልፀዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት የተከበሩ አቶ ኢብራሂም ኡስማን በበኩላቸው ሄር ኢሴ በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን በማግኘቱና በመመዝገቡ የተሰማቸውን ደስታ በመግለፅ ለዚህ ድል መሳካት የበኩላቸውን ሚና ለተወጡ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመድረኩ የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፈቲያ አደን፣ የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅ/ጽ/ቤት ሀላፊ የተከበሩ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ፣ የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት የተከበሩ አቶ ኢብራሂም ኡስማን፣ አባገዳዎች ጉጋዞች እንዲሁም በርካታ ቁጥር ያላቸው የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል

በኤደን ሳሙኤል

ፎቶ:- አገኘሁ ሸዋረጋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *