በድሬዳዋ አስተዳደር የመልካም አስተዳደር እና ቅሬታ አፈታት ዙሪያ የተከናወኑ ስራዎችን ድጋፍና ክትትል ማድረግ አላማ ያደረገ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የተውጣጣ ልዑክ በድሬደዋ ቆይታ አድርጓል።
በአስተዳደሩ የተሻለ አፈፃፀም ያሳዩ የሴክተር ተቋማትና ወረዳዎች በመልካም አስተዳደር የችግር አፈታት እና ቅሬታ ዙሪያ ያከናወኑትን ስራዎች ከፌዴራል ለተገኙት አካላት በዝርዝር በማቅረብ ውይይት ተካሂዷል።
ልዑኩ የድሬዳዋ አስተዳደር ከህዝቡ ለሚቀርቡ ቅሬታዎች ምላሽ አሰጣጥ ሂደት እንዲሁም ህዝቡን ያማከለ የአሰተዳደር ችግሮች ልየታና ጥናት አሰራር ያሉ ተሞክሮዎችን መገምገሙን በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ክትትል፣የቅሬታና አቤቱታ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍቅሩ ወርቁ ገልፀዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር የከንቲባ ጽ/ቤት እና የካቢኔ ጉዳዮች ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ሰዓዲያ አዋሌ አስተዳደሩ ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልፀው በአስራርና በአደረጃጀት ዘርፉን በማጠናከር ወጥና የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር የመልካም አስተዳደር ችግሮች ጥናት ፣ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ዘለቀ በበኩላቸው በተቋማት እና ወረዳዎች ላይ ከማህበረሰቡ ጋር በእቅድ ውይይት ችግሮች እንዲፈቱ እየተደረገ እንደሚገኝ ፤ ከቅሬታ አፈታት ስርዓት ጋር በተያያዘም የቴክኖሎጂ ሶፍትዌር በማበልፀግ ባለጉዳዮች ላይ የሚገጥሙ እንግልቶችን ለመቀነስ እየተሰራ እንደሆነ አስረድተዋል


