ድሬዳዋ ከተማ ወደ ቀድሞ እድገቷና ልማቷ ለመመለስ የነዋሪዎቿን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ በሚቻልበት ሀኔታዎች ዙሪያ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች እና ከፍተኛ ግብር ከፋዮች የተሳተፉበት የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡ የፓናል ውይይቱም በአስተዳደሩ ተጀምሮ የነበረው የታክስ ንቅናቄ አካል ነው፡፡
ለፓናል ውይይቱ የመነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊሲ ጥናት ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ተሰማ ባቀረቡት ሰነድም በአስረዳደር ደረጃ በ2010 ዓ.ም የነበረውን አጠቃላይ ገቢን የመሰብሰብ አቅም የነበረበትን የአፈፃፀም ደረጃ፣ ያጋጠሙ ችግሮችን እንዲሁም በቀጣይ መደረግ የሚገባቸውን ተግባራት አመላክተዋል፡፡ በቀረበው ሰነድም በአስተዳደር ደረጃ ምንም እንኳን የሚሰበሰበው የገቢ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢሆንም የሚጨምርበት ፍጥነት ግን እየቀነሰ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ከተሞች አሁን በደረሱበት የእድገት ደረጃ እስከ 75% የሚሆነውን የራሳቸውን ወጪ በራሳቸው ገቢ መሸፈን ያለባቸው ቢሆንም በ2010 ዓ.ም በአስተዳደር ደረጃ የነበረው አፈፃፀም ግን 45% ብቻ እንደነበርና ከዚህም ከታክስ የተሰበሰበው 8.5% መሆኑን ነው የተገለፀው፡፡
በአስተዳደሩ የሚሰበሰበው ገቢ ለመቀነሱ በርካታ ምክኒያቶች የተነሱ ሲሆን የግብር ከፋዮች የግንዛቤ ማነስ፣ ህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ መስፋፋት፣ የመንግስት ቁጥጥር ማነስና የህብረተሰቡ ደረሰኝ የመጠየቅ ባህል አናሳ መሆን፣ የገቢ አሰባሰቡ በጥናት ላይ የተመሰረተ አለመሆን፣ በአስተዳደሩ የሚገኙ ግዙፍ ፋብሪካዎች ከሚያስገቡት ገቢ አስተዳደሩ ተጠቃሚ መሆን አለመቻሉና ሌሎች በርካታ ተግዳሮቶች በተሳታፊዎች ተነስተዋል፡፡
በውይይቱ ሀሳብ የሰጡት የድሬዳዋ አስተዳደር መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቂያስ ታፈሰ እንደተናገሩት ግብር ከፋዮች ግብርን በአግባቡ መክፈል የሞራል፣ ህጋዊና ሀይማኖታዊ ግዴታም ጭምር መሆኑን በመገንዘብ ግብራቸውን በወቅቱና በአግባቡ በመክፈል በምድርም በሰማይም ተጠያቂ ከመሆን ተላቀው ተሸላሚ ለመሆን መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
ለተነሱ ሀሳቦች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡት የድሬዳዋ አስተዳደር ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሱልጣን አሊዬ በበኩላቸው የተነሱት ችግሮች መኖራቸውን ገልፀው የአስተዳደሩን ገቢ የመሰብሰብ አቅም ለማሳግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንና የግብር አሰባሰብን ስርዓትን ለማዘመንና ቀልጣፋ ለማድረግ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተሻለ ቴክኖሎጂን እንዲጠቀም ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑንና የተቋሙን ሠራተኞች አቅም የመገንባት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይም በአስተዳደር ደረጃ መሰብሰብ ሲገባቸው የማይሰበሰቡ ገቢዎችን በተመለከተ በአስተዳደሩ ከተማ ስራ አስኪያጅ ፅ/ቤት በኩል ከፍተኛ የሆነ ክፍተት የሚስተዋል በመሆኑ ችግሩን ለመፍታትም ተቋሙን በማፍረስ በአዲስ እንዲዋቀር የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በከተማችን ከሚገኙት ታላላቅ ኢንዱስትሪዎች ከሚገኘው ገቢም አስተዳደሩ ተጠቃሚ እንዳይሆን የሚያደረጉ ክልከላዎች እንዲነሱ ለማድረግና አስተዳደሩ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዲያገኝ ከቻርተሩ ጀምሮ ማስተካከያዎችን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ሱልጣን ተናግረዋል፡፡ አቶ ሱልጣን አክለውም የድሬዳዋ ህዝብ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተደደር ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ ብሎም የድሬዳዋን ልማትና እድገት ማረጋገጥ እንዲቻል የአስተዳደሩ ግብር ከፋዮች ግብርና ታክስን በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡


